ጋዜጠኞችንና የፖለቲካ እስረኞችን ለማሰፈታት ሸምግልና እየተካሄደ ነው

ነሀሴ ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ የሚመራው ራሱን “የኢትዮጽያ የሸማግሌዎች ኀብረት” በሚል የሚጠራው ቡድን ትላንት ነሐሴ 16 ቀን 2004 ዓ.ም፣  ማምሻውን በሸራተን ሆቴል በሰጠው መግለጫ “ሰላም ወዳድ ነበሩ” ያላቸውን በአቶ መለስ ዜናዊ ፤ዜና ዕረፍት የተሰማውን ሐዘን በገለጸበት መግለጫው በመጪው መስከረም ወር በዓልን አስታኮ ለእስረኞች ምህረት ለማድረግ ጠ/ሚኒስትሩ ቃል ገብተው ነበር ሲል ተናገረ።

ፕሮፌሰር ኤፍሬም አሁን በእስር ላይ ባሉት ወገኖች ጉዳይ ጠ/ሚኒስትሩን አነጋግረው “በመስከረም ኑ፣አዲስ ዓመትን ተመርኩዘን ብዙ ችግሮችን እንፈታለን” የሚል ቃል እንደገቡላቸው አስታውሰው፣ተተኪው ጠ/ሚኒስትርም ይህንኑ

አክብረው ተግባራዊ እንደሚያደርጉ እንደማይጠራጠሩ ገልጸዋል፡፡

የኮሚቴው አባል የሆኑትና በቅርቡ የዕርቅ ሰነድ ፈርመው ወደአገር ቤት ከገቡት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አባቢያ አባጆቤ አባዱላ በበኩላቸው ቡድኑ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን፣በጠ/ሚኒስትሩ በኩልም

እስር ቤቶችን ባዶ አደርግላችሃለሁ እስከማለት ቃል እንደተገባላቸው አስታውሰዋል፡፡ከአሁኑ ተጠባባቂ ጠ/ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ለመነጋገርም ቀጠሮ ጠይቀው ምላሸ እየተጠባበቁ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ፓስተር ዳንኤል ገ/ስላሴ “የፖለቲካ እስረኞች” የሚለውን የአቶ አባቢያ ገለጻ በማረም “ነገሩ በፖለቲካ ጀምሮ በወንጀል የሚከሰሱ በመሆናቸው በወንጀል የተከሰሱ” እንዲባል በመጠየቅ እርማት ሰጥተዋል፡፡ባለፉት አምስት ዓመታት

80ሺ ያህል እስረኞች በኢትዮጽያ በይቅርታ እንደተፈቱ ያስታወሱት ፓስተር ዳንኤል፣ይህ በዓለም ላይ ወደር የማይገኝለት እርምጃ መሆኑን በማድነቅ፤ ይህን አድርገዋል ያሉዋቸውን ለጠ/ሚኒስትር መለስ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡

“ይፈታሉ የተባሉት እስረኞች አሁን በእስር ላይ ያሉ ጋዜጠኞችና የፖለቲካ መሪዎችን ይጨምራል ወይ?” በሚል ተጠይቀው ፕሮፌሰሩ ሸምግልናችን እከሌ ከእገሌ አይልም የሚል ድፍን ያለ ምላሸ ሰጥተዋል፡፡

አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ  በኢትዮጽያ ላሉ ችግሮች ሸምግልና ወሳኝ ሥራ መሆኑን በማስታወስ፣የሸማግሌዎቹ ቡድን ሥራ ከመንግስት ይልቅ በዚያኛው ወገኖች እየተሸረሸረ መጥቶአል ሲል ወቀሳ ሰንዝሮአል፡፡አንዳንድ በሸምግልና የተፈቱና

ቁጥራቸው ሁለት በመቶ የማይሞሉ ሰዎች በአሜሪካና አውሮፓ ቁጭ ብለው የሚያደርጉት አሉታዊ ነገር ጉዳት እያመጣብን ነው፡፡መንግስት “ይህው እናንተ ያስፈታቹሃቸው ሰዎች እንዲህ እያደረጉ ነው፡፡እናንተ ማስፈታት ብቻ ነው እንዴ

አቅማችሁ ሲል ይወቅሰናል፡፡ይህ ሁኔታ ስራችን ወደፊት እንዳንገፋ አንድ እንቅፋት በመሆኑ ጉዳዩን እንዲስተከካከል በእናንተ በኩል መልዕክታችን ይድረስልን” ሲል  ጋዜጠኞችን ተማጽኗል፡፡ሆኖም ይደረጋል ያለው አሉታዊ ነገር ምን እንደሆነ በግልጽ ያስረዳው ነገር የለም፡፡

የሸማግሌዎቹ ቡድን በዕርቅና በሸምግልና መንገድ ይዞአቸው ብዙ ርቀት ከተጓዘባቸው ጉዳዮች መካከል በኦነግና በመንግስት እንዲሁም በኦጋዴን ነጻነት ግንባርና በመንግስት መካከል ያለውን ችግር በሸምግልና መፍታት እንደሚገኝበት ጠቅሰው የተጀመሩት ጥረቶች የተጓተቱት በፋይናንስ እጥረትና በፖለቲካ ፓርቲዎቹ መካከል አንዳንድ መከፋፈሎች ስለነበሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

____________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide