ግንቦት ፳፩ ( ሃያ አንድ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአማራ ማስ ሚዲያ ውስጥ ጋዜጠኛ የሆነውና በድፍረት በሚሰነዝራቸው ትችቶች የሚታወቀው ጋዜጠኛ ፍቅረማርያም አያናው ከስራ መታገዱንና የመንግስትን ስም በማጥፋት ሊከሰስ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል።
ጋዜጠኛ ፍቅረማርያም ከስራ መታገደኑን ወደ መስሪያ ቤት ሲገባ መከልከሉን ኢሳት ለማረጋገጥ ችሎአል። ፍቅርማርያም ጥልቅ ተሃድሶ በሚል በአማራ ክልል የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ለጋዜጠኞች በተዘጋጀ ዝግጅት ላይ፣ የህወሃትን የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ እና የህወሃት የደህንነት አባላትና የጸጥታ ሃይሎች በዜጎች የፈጸሙትን ግፍ ኢሳት ሙሉውን አቅርቦ ማሰማቱ ይታወቃል።
ፍቅረማርያም በወቅቱ “ ጣሊያን በዚህ ወቅት ቢመጣ አንቀጥቅጦ ይገዛናል፣ አንድ አይደለንም፣ ተከፋፍለናል። ትናንት የወንድሞቻችን ደም ፈሷል፣ የትናንት መሪዎች አገር የሚያጠፉ አልነበሩም” የሚል የብሄር ፖለቲካውን የሚተች ንግግር አቅርቦ ነበር።
ፍቅረማርያም ከስራ የታገደው በዚህ ንግግሩ ነው የሚሉ ጋዜጠኛውን በቅርብ የሚያውቁ ሰዎች ቢኖሩም፣ ሌሎች ሰዎች ደግሞ የታገደው በቅርቡ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ባወጣው ጽሁፍ ነው ይላሉ።
ጋዜጠኛ ፍቅረማርያም በፌስቡክ ገጹ ላይ “ የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት የፕሮግራም ማሻሻያ ሊያደርግ ነው ፡፡ ታዲያ ይህን ማሻሻያ እንዲያደርጉ ሃላፊነት የተጣለባቸው ጋዜጠኞች በጎርጎራ መዝናኛ እየተዝናኑ ማሻሻውን በመስራት ላይ ናቸው፡፡ ምን ይዘው ይመጡ ይሆን? በሄዱት ሰዎች አቅም ይወሰናል፡፡ የሄዱት ሰዎች የተመረጡበት መስፈርት ግልጽ አይደለምና ብዙ አልጠብቅም፡፡ ለሰው ልጅ ህይወት ቅርበት ያላቸው/ በተለይ ለኛ ለኢትጵያውያን ጠቃሚ የሆኑት መረጃዎች የትኞቹ እንደሆኑ ይታወቃሉ፡፡ አድማጭ ተመልካቾች ፕሮገራሙን ከታደሙ በኋላ ምን ያድርጉ? ሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ በተጨማሪም ለውሳኔ የሚረዳ፣ የባህሪ ለውጥ ሚያመጣ ካልሆነ ከማደንቆር የዘለለ ፋይዳ ሊኖረው አይችልም፡፡ ይህን የሚችለው ግን ወጥቶ ወርዶ የዘገበ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ምክንያቱም ችግሩን በቅርበት ያውቀዋልና፡፡”
ሲል ጽፎ ነበር።