ኢሳት (ግንቦት 16 ፥ 2009)
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእስር ላይ በሚገኘው ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ላይ በተመሰረበት የወንጀለኛ ክስ ረቡዕ የጥፋተኝነት ብይን አስተላለፈ።
የነገረ-ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ጌታቸው በመጀመሪያ ዙር የሽብተኛ ወንጀል ክስ ተመስርቶ የቆየ ቢሆን፣ ከሳሽ አቃቤ ህግ ክሱን ወደ መደበኛ ወንጀል ክስ ዝቅ ማደረጉ ታውቋል። ከሳሽ አቃቤ ህግ ጋዜጠኛው በአሜሪካ ሃገር የሚገኘው ጋዜጠኛ አበባ ገላው ከአምስት አመት በፊት በሟች ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ላይ ተቃውሞ በገለጸ ጊዜ ድጋፍን በፌስ ቡክ አስተላልፏል ሲል በክሱ ማመልከቱን አዲስ ስታንዳርድ መጽሄት ዘግቧል።
የፌዴራል ከሳሽ አቃቤ ህግ በመጀመሪያ ዙር የመሰረተውን የሽብርተኛ ወንጀል ክስ ወደ መደበኛ ወንጀል ክስ በመቀየር ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ላይ መቀመጫውን በውጭ ካደረገና በሽብተኛ ወንጀል ከተከሰሰ አካል ጋር ግንኙነት (ወይም መልዕክት ተለዋውጧል) ሲል ክሱን አሻሽሎ ማቅረቡ ታውቋል።
ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ረቡዕ ጋዜጠኛውን ጥፋተኛ ሲል ብይን ሰጥቷል።
ፍርድ ቤቱ ከነገ በስቲያ አርብ የቅጣት ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
የጋዜጠኛው ጠበቃ አቶ አመሃ መኮንን ደንበኛቸው እስከ 10 አመት የሚደርስ የእስር ቅጣት ሊተላለፍበት እንደሚችል ገልጸዋል።
ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ከአንድ አመት በፊት በጸጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር መዋሉ የሚታወስ ነው። የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት በቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አቶ ዮናታን ተስፋዬ በተመሰረተበት የሽብርተኛ ወንጀል ክስ ተመሳሳይ የጥፋተኝነት ብይን ሰጥቷል።
አለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት CPJ እና ሌሎች መሰል አካላት የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞችን ለእስር በመዳረግና በማዋከብ ግንባር ቀድም መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።
በአሁኑ ወቅትም 15 ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንደሚገኙ ለመረዳት ተችሏል። መንግስት ጋዜጠኞችን በተለይም የሽብርተኛ ወንጀል ክስ በመመስረት ለእስር ቢዳርጋቸውም አለም አቀፍ ተቋማት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሌሎች ጋዜጠኞችን አለም አቀፍ ሽልማት ሲሰጡ ቆይተዋል።