ጥቅምት ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-18 የእስር አመታት በግፍ ተፈርዶበት በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የፔን ካናዳ የ2015 አሸናፊ ሆነ መመረጡን ድርጅቱ አስታውቋል።
ለብዙዎች የዲሞክራሲ ሃይሎች የጽናት ምልክት ተደርጎ የሚቆጠረው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ በሽብር ወንጀል ተከሶ ያለፉትን ሶስት አመታት በእስር ቤት አሳልፏል። የእስክንድር ስራዎቹ ድንበር እና ባህል ተሻጋሪ ናቸው በማለት ያወደሰው ድርጅቱ፣ 5 ሺ ዶላር የሚያሸልመው ሽልማት በ36ኛው የአለማቀፍ ጻሃፊዎች ቀን ላይ ይበረከትለታል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ቡድን የእስክንድርን መታሰር አለማቀፍ ህግን የጣሰ መሆኑን በመጥቀስ እንዲፈታ መጠየቁን መግለጫው አውስቷል።
ጋዜጠኛ እስክንድር ከሶስት አመታት በፊት የፔን ባርባራ ጎልድ ስሚዝ ፍሪደም ቲ ራይት ፣ አምና ደግሞ ጎልደን ፔን አዋርድ ኦፍ ፍሪደም አሸናፊ መሆኑ ይታወቃል። በምርጫ 97 ወቅት እስክንድር ከቅንጅት መሪዎች ጋር አብሮ ታስሮ የተለቀቀ ሲሆን፣ ቀድም ብሎም ከስራው ጋር በተያያዘ ከ5 ጊዜ በላይ ታስሯል። በስልጣን ላይ ያለው ገዢ ፓርቲ የጋዜጣ ፈቃድ የከለከለው እስክንድር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የስርዓት ለውጥ አይቀሬ መሆኑን ማስረጃዎችንና ምልከታውን ተንተርሶ የተለያዩ ጽሁፎችን በማህበራዊ ድረገጾች ላይ ጽፏል።