ታኀሳስ ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በእነ ዘላለም ወርቅአገኘሁ የክስ መዝገብ በመከላከያ ምስክርነት የተጠቀሰውን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን በምስክርነት እንደማያቀርበው የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ለልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በደብዳቤ አሳውቋል።
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የ18 አመት ፅኑ እስራት የተፈረደበት በመሆኑና ከአሁን ቀደም ምስክር ሆኖ ከማረሚያ ቤቱ ወጥቶ መስክሮ ስለማያውቅ ለምስክርነት ለማቅረብ እንቸገራለን የሚል ደብዳቤ ማረሚያ ቤቱ ታህሳስ 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ለልደታ ፍርድ ቤት መላኩን ተከትሎ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ለምስክርነት ሳይቀርብ ቀርቷል።
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከአንድ አመት በፊት ከ6 ሰዓት እስከ 6 ሰዓት ተኩል ለ30 ደቂቃዎች ሲጠየቅ የነበረውን ሕገ መንግስታዊ መብቱ በመጣስ ወሕኒ ቤቱ በአሁኑ ሰዓት እንዳይጠየቅ ከማድረጉም በተጨማሪ በተደጋጋሚ የታሰረበትን ክፍል በመፈተሽ መፅሃፍ ቅዱስ ሳይቀር እንዳያነብ መከልከሉን ነገረ – ኢትዮጵያ አክሎ ዘግቧል።