ሐምሌ ፲ ( አሥር ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከሕግ አግባብ ውጪ በኮማንድ ፖስቱ ተይዘው በእስር ሲሰቃዩ የነበሩት ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ እና አቶ ዳንኤል ሺበሺ እያንዳንዳቸው የ50 ሺህ ብር ዋስትና እንዲያቀርቡ ሲል የቦሌ ክፍለ ከተማ ከፍተኛው ፍ/ቤት ሀምሌ 10 ቀን 2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት ብይን ሰጠ።
ፍርድ ቤቱ ሁለቱም ተከሳሾች ያቀረቡትን ይግባኝ ተቀብሎ የዋስትና መብታቸውን ከመቀበሉ በተጨማሪ ጉዳያቸው በዝግ ችሎት እንዲታይ፣ ክርክሩ በቀደመው ችሎት እንዲቀጥል፣ የፍርዱ ሂደቱ እስኪያልቅ ከአገር እንዳይወጡ፣ ማረሚያ ቤቱም የፎቶ መራጃቸውን ለብሔራዊ ደኅንነት እንዲልክ ውሳኔ ተላልፏል፡፡ በተጨማሪም አቤቱታ አቅራቢዎች በዝግ ችሎት መታየት የለበትም ብለው ያቀረቡትን ውድቅ አድርጎ በውሳኔው እንዲፀና በይኗል።
ከሕዳር 08 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ በእስር ላይ ያሳለፉት ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ እና አቶ ዳንኤል ሺበሺ ይህን ዜና እስካጠናቀርንበት ድረስ የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ይውጡ አይውጡ አልታወቀም።