ጋዜጠኛ ታደሰ እንግዳው አረፈ

ሐምሌ ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ጀርመን ድምጽ ራዲዮ የአዲስ አበባ ወኪል የሆነው ጋዜጠኛ ታደሰ እንግዳ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

ተወዳጁ  ጋዜጠኛ ይህን ዓለም የተሰናበተው፤ ትላንት ማምሻውን በደረሰበት   ድንገተኛ  የመኪና አደጋ ነው።

ደቼ ቨለ እንደዘገበው ፤ጋዜጠኛ ታደሰ አደጋው የደረሰበት፤ ከአዋሳ የኒቨርሲቲ ዘንድሮ ትምህርቱን ባጠናቀቀ በወንድሙ ምረቃ ፕሮግራም ላይ ተካፍሎ ወደአዲስ አበባ በመመለስ ላይ ሳለ ነው።

በአደጋው ከታደሰ በተጨማሪ ለምርቃቱ ወደ አዋሳ ሄዶ የነበረ ሌላ ወንድሙም የሞተ ሲሆን፤ ከአዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተመረቀው ደግሞ ክፉኛ የመቁሰል አደጋ ደርሶበት ህክምና እየተከታተለ ይገኛል።

ታደሰ ባጋጠመው ድንገተኛ አደጋ በተለይ የሥራ ባልደረቦቹ የሆኑት የጀርመን ድምጽ ጋዜጠኞች  ከመደናገጣቸውም ባሻገር እጅግ ጥልቅ በሆነ የሀዘን ስሜት ውስጥ ተውጠውና በእንባ ሲቃ ታፍነው በህልፈቱ ዙሪያ ሲወያዩ ተደምጠዋል።

ታደሰ በተለይ ከ1990 ዓመተ ምህረት ወዲህ በ ኤሌክትሮኒክ ሚዲያው ዘረፍ በፍጥነት እያደገ የመጣ ጎበዝ ጋዜጠኛ እንደሆነ ባልደረቦቹ መስክረውለታል።

በምርጫ 97 ጊዜ ቅንጅት አይሎ በወጣበት በዚያ የትኩሳት ወቅት፤ እጅግ ውጥረት በተሞላበት ሁኔታ ከሁሉም ወገን ያሉትን መረጃዎች ሚዛናዊ በሆነና በተሟላ ሁኔታ በማቅረብ ሙያዊ ግዴታውን በብቃት የተወጣ እንደነበርም ተገልጿል።

በፍርድ ቤት ችሎት፤በፖለቲካው፣በማህራዊ ጉዳዮች እና በስፓርቱ ዘርፍ ጭምር ሁለ-ገብ ዘገባዎችን በብቃትና በፍጥነት በማቅረብ   የሚታወቀው  ታደሰ፤ከባልደረቦቹ በተጨማሪ በደቸቨለ አድማጮች ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ጋዜጠኛ ሆኖ ቆይቷል።

የታደሰ እና የሌለኛው ሟች ወንድሙ የቀብር ሥነ-ስርዓት በጎንደር ከተማ ቤተሰብ፣ ጋደኛ እና ወዳጅ ዘመድ በተገኘበት ዛሬ ተፈጽሟል።

የ39 ዓመት ጎልማሳ የሆነው ጋዜጠኛ ታደሰ፤ ባለትዳር እና የሦስት ልጆች አባት ነበር።

በጋዜጠኛ ታደሰ እንግዳ ሞት ሀዘን  የበረታባቸው ቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹ ፣  የሥራ አጋሮቹ እና አድናቂዎቹ በሙሉ  መጽናናት እንዲሆንላቸው ፣የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና ራዲዮ ዝግጅት ክፍል ባልደረቦቸ በሙሉ ልባዊ ምኞታቸውን ይገልፃሉ።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide