ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ተከሰሰ

ነሀሴ ፬ (አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በማስተዋል የህትመትና ማስታወቂያ ሥራ ድርጅት አማካይነት በየሳምንቱ ዓርብ ዕለት እየታተመ ለንባብ የሚበቃው የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝና ድርጅቱ ሶስት ክሶች ዛሬ ተመሰረቱባቸው፡፡

የፌዴራሉ አቃቤ ህግ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 16ኛ የወንጀል ችሎት ክስ የመሰረተባቸው በፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ እና በማስተዋል የህትመት እና ማስታወቂያ ስራ ድርጅት ላይ ነው።

አቃቤ ህግ በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ የመሰረታቸው ሶስት ክሶች ማለትም  ወጣቶች በአገሪቱ መንግስትና ህገ መንግስታዊ ስርአቱ ላይ እንዲያምጹ የመገፋፋትና ግዙፍ የሆነ የማሰናዳት ተግባር፣  የሀገሪቱን መንግስት ስም ማጥፋት እና የሀሰት ውንጀላ እንዲሁም የሀሰት ወሬዎችን በማውራት ህዝብን በማነሳሳት ወይም አስተሳሰባቸውን ማናወጥ የሚሉ ናቸው።

የክስ መዝገቡ እንደሚያስረዳው በጋዜጣው የነሃሴ 23 ቀን ቅጽ 04 ቁጥር 149 እትም ላይ “ሞት የማይፈሩ ወጣቶች” በሚል ርዕስ የአጼ ሃይለስላሴን ስርአት ወጣቶች እንዴት እንዳፈረሱት እና አሁን ያለው ስርአትም አፋኝ እና ጨቋኝ መሆኑን በመግለጽና አሁንም ሞት የማይፈሩ ወጣቶች መኖራቸውን ጠቅሶ በአረቡ አለም የተከሰቱ የህዝብ አመጾችን በሀገራችን እንዲተገበር በማሰብ ወጣቶች አደባባይ ለአመጽ እንዲወጡ በጽሁፍ ቀስቅሷል ይላል።

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ መከሰሱን የሰማው ከሬዲዮ ፋና መሆኑ ታውቋል።

____________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide