ኢሳት (ኅዳር 30 ፥ 2009)
በዝዋይ እስር ቤት በእስር ላይ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በእስር ቤቱ አለመኖሩንና ያለበት ቦታ እንደማይታወቅ የጋዜጠኛውን ጉዳይ የሚከታተሉ አካላት ለኢሳት ገለጹ።
የጋዜጠኛው ቤተሰቦች በበኩላቸው የማህበራዊ ድረገጾች ባሰራጩት መረጃ ዝዋይ እስር ቤት ተመስገንን ለመጠየቅ ሁለት ቀን ቢሄዱም፣ በእስር ቤቱ ተመስገን የሚባል የመንግስት እስረኛ አናውቅም የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው አረጋግጠዋል።
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በማፈላለግ ላይ ያሉ የቤተሰቡ አባላት አዲስ አበባ በሚገኘው የማዕከላዊ ምርመራ እስር ቤት ቢሄዱም፣ “ተመስገን የሚባል የለም” መባላቸውን አስታውቀዋል።
ለሶስት ቀናት ጋዜጠኞው ያለበትን ቦታና ሁኔታ ለማወቅ ያልቻሉ የቤተሰቡ አባላት መንግስት ተመስገን ደሳለኝ ያለበትን ሁኔታ እንዲያሳውቋቸው አክለው ጠይቀዋል።
የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በከሳሽ አቃቤ ህግ የተመሰረተበትን የስም ማጥፋት ሃስተኛ መረጃ ማሰራጨት መነሻ በማድረግ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከሁለት አመት በፊት ጋዜጠኛው በሶስት አመት እስራት እንዲቀጣ መወሰኑ ይታወሳል።
ጋዜጠኛው በዚሁ በእስር ቤት በነበረ ጊዜ የጤና መታወክ እክል አጋጥሞት ህክምና እንዲያገኝ ተደርጎ እንደነበር በወቅቱ መገለጹም የሚታወቅ ነው።