(ኢሳት ዜና–ሕዳር 22/2010)
በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን በጋዜጠኝነትና በስራ አስኪያጅነት ለረጅም አመታት ያገለገለው ጋዜጠኛ ሳሙኤል ፈረንጅ ከዚህ አለም በሞት ተለየ።
ሳሙኤል ፈረንጅ ከጋዜጠኝነቱ ሌላ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት በተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች ላይ ማገልገሉ ታውቋል።
አቶ ሳሙኤል ፈረንጅ በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በጋዜጠኝነትና በስራ አስኪያጅነት ለረጅም አመታት አገልግሏል።በሌሎች የመንግስት ተቋማትም በከፍተኛ የሃላፊነት ቦታዎች ላይ አገልግለዋል።
ከአባቱ ከቀኝ አዛማች ፈረንጅና ከእናቱ አበበች ገመዳ በ1929 በወለጋ ነቀምት የተወለደው ሳሙኤል ፈረንጅ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው በደምቢዶሎና በአዲስ አበባ ተፈሪ መኮንን መሆኑን የህይወት ታሪኩ ያስረዳል።
የከፍተኛ ትምህርቱንም በጅማ እርሻ ኮሌጅ መከታተሉ ታውቋል።
ሳሙኤል ፈረንጅ በቀዳማዊ ሃይለስላሴ ዘመን በነበረው የጋዜጠኝነት ብቃትና ፍላጎት ቀዳማዊ ሃይለስላሴ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አድርገው ሾመውታል።
የደርግ መንግስት ስልጣን ከተረከበ በኋላም በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በሃላፊነት አገልግሏል።
በፍትህ ሚኒስቴር፣በእርሻ ሚኒስቴርና በመሬት ይዞታ እንዲሁም በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ማገልገሉንም ከታሪኩ መረዳት ተችሏል።
ጋዜጠኛ ሳሙኤል ሀገሩን በስደት ለቆ ከወጣ በኋላ በጀርመን፣በጣሊያን እንዲሁም ሕይወቱ እስካለፈበት ድረስ በካናዳ ቶሮንቶ ለረጅም አመታት ኖሯል።
የሀገሩን ስም በማንሳትና ህዝቦች ተቀራርበው ለሀገራቸው አንድነት እንዲተጉ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንም ለማወቅ ተችሏል።
ጋዜጠኛ ሳሙኤል ከ17 ሀገራት ሜዳሊያ የተሸለመ ሲሆን ከሀገሩም የክብር ኮከብ የመኮነንነት ደረጃ ኒሻን ተሸልሟል።
ከጣሊያንና ከኦክላህማ የክብር ዜግነት ማግኘቱም ታውቋል።
እንዲሁም ለልዕልት ዲያና የጻፈው ግጥም አሸናፊ በመሆኑ ከአሜሪካ ብሔራዊ የገጣሚያን ቤተመጻህፍት ትልቁ ሽልማት ተበርክቶለታል።
ሳሙኤል ፈረንጅ መሰንበት ደጉና የጥፋት መንትዮች የተሰኙ ሁለት መጽሀፍትንም ለአንባብያን አበርክቷል።
የ88 አመቱ ጋዜጠኛ ሳሙኤል ፈረንጅ 7 ወንዶች፣ አንድ ሴት ልጅ፣ 7 የልጅ ልጆችና አንድ የልጅ ልጅ ልጅን ማየት ችሏል።