ጋዜጠኛ ሃብታሙ ምናለ የአልሸባብ የቡድን ሴል ነህ ተብሎ መታሰሩ ተዘገበ

ሐምሌ ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ፣ የቀዳሚ ጋዜጣ ስራ አስኪያጅና የሚሊዮኖች ድምጽ ጋዜጣ ሪፖርተር የነበረው ሃብታሙ ምናለ ” የአልሸባብ የሽብር ወንጀል ቡድን ሴል ነህ” በሚል ተጠርጥሮ መገናኛ አካባቢ በሚገኘው አምቼ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ እንደሚገኝ ገልጿል። ሃብታሙ፣ “የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በሚገኙበት ስብሰባ ላይ የሽብር ወንጀል ልትፈጽም በማሰብ ስትንቀሳቀስ ነበር በሚል ከሌሎች 44 ተጠርጣሪዎች ጋር መታሰሩን” እንደገለጸት ዘግቧል።
ከሲ.ኤም.ሲ አካባቢ የተያዙ ሰባት የሶሪያ እና ሁለት የኖርዌይ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ሶማሌያውን ታስረው እንደሚገኙ የዘገበው ኤልያስ፣ የተቀሩት ደግሞ ቦሌ ሚካኤል አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ሶማሌያውን ሲሆኑ፣ አንዳቸውንም እንደማያውቃቸው እና በአይኑም ያያቸው አብረው ከታሰሩ በኋላ መሆኑን ሃብታሙ እንደነገረው ገልጿል፡፡
ሃብታሙ ከቤቱ አንድ ዴስክ ቶፕ ኮምፒውተር እንደተወሰደበት ገልጾ፣ ሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ ለተጨማሪ ምርመራ የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ እንደተጠየቀበት እና ሐምሌ 20 ቀን 2007 ዓ.ም በድጋሚ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ዘገባው አመልክቷል።
ሀብታሙ፣ የቦሌ ሚካኤል ቤ/ክርስቲያን አገልጋይ እንዲሁም የሰንበት ት/ቤት መንፈሳዊ አስተማሪ መሆኑን ጋዜጠኛ ኤልያስ በዘገባው ጠቅሷል።
በሌላ ዜና ደግሞ እየታፈኑ የሚታሰሩ የቀድሞ የአንድነት አባላት ቁጥር እየጨመረ መምጣጡን የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የሰሜን ጎንደር ዞን የአንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ የነበሩትና የጎንደር መምህራን ኮሌጅ መምህር አቶ ሃምሌ 1 ቀን ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ መኖሪያ ቤታቸው ድረስ ዘልቀው በገቡ ታጠቂ ታፍነው ተወስደዋል፡፡
ከአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ በInformation systems የተመርቁ እና በጎንደር መምህራን ኮሌጅ የICT ትምህርት ክፍል ውስጥ በመምህርነት በማገልገል ላይ የነበሩት አቶ አለላቸው፣ ከመኖሪያ ቤታቸው ያለማንም ፈቃድና ዕውቅና ሙሉ ትጥቅ በታጠቁ ፖሊሶች ተወስደዋል። ከመኖሪያ ቤታቸው ከተወሰዱ በኋላም እርሳቸው በሌሉበት መኖሪያ ቤታቸው በታጠቁ ቡድኖች ሲጠበቅ አድሮ፤ በበነገታው ጧት አቶ አለላቸው በካቴና ታስረው ቤታቸው ድረስ በታጣቂዎች ታጅበው ከመጡ በሁዋላ ብርበራ ተካሂዷል።
በሌላ በኩል ደግሞ የ9 ወር ህጻን ልጅ ጥላ የታሰረቸው የቀድሞው የኢህአዴግ አባልና የምእራብ አርማጭሆ የሴቶች ሃላፊ የነበረቸው፣ በሁዋላ ላይ ኢህአዴግን በመተው አንድነት ፓርቲን የተቀላቀለችው፣ ወ/ሮ አስቴር ስዩም ማእከላዊ እስር ቤት ገብታ የሽብረተኝነት ክስ ተመስርቶባታል። ባለቤቷ አቶ በለጠ ጌትነት ለኢሳት እንደገለጸው፣ ወ/ሮ አስቴር አንድነት ፓርቲ ከፈረሰ በሁዋላ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረጓን አቁማ ነበር። ባለቤቱ በሽብር ወንጀል መከሰሷ እንቆቅልሽ እንደሆነበት አክሎ ገልጿል።