(ኢሳት ዜና –ሐምሌ 10/2009) አንጋፋው ጋዜጠኛና ደራሲ ነጋሽ ገብረማርያም በ93 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለዩ።
ስርአተ ቀብራቸው ሐምሌ 11/2009 በጉርድ ሾላ ሳህሊተ ምህረት ቤተክርስቲያን እንደሚፈጸም ተነግሯል።
አንጋፋው ጋዜጠኛና ደራሲ ነጋሽ ገብረማርያም የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥንን በመምራትና የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆነው አገልግለዋል።
በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትና በሬዲዮ እንዲሁም በቴሌቪዥን በጋዜጠኝነት ሙያ ሲሰሩ በሙያው ዘመናዊ ትምህርት ከተማሩ የቀድሞ ጋዜጠኞች አንጋፋ እንደነበሩ የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።
ጋዜጠኛ ነጋሽ ገብረማርያም ሴተኛ አዳሪዋ፣የአዛውንቶች ክበብና የድል አጥቢያ አርበኞች የተባሉ ድርሰትና ተውኔቶች ጸሃፊ ናቸው።
በሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት በጨርጨር አውራጃ በሀብሮ ወረዳ ልዩ ስሟ መቻራ በምትባል አካባቢ በ1917 የተወለዱት አንጋፋው ጋዜጠኛ ነጋሽ ገብረማርያም አዲስ ዘመን እልታዊ ጋዜጣ እንዲሆን በማድረግና የወሬ ነጋሪ የሚባለውን መስሪያ ቤትም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዲባል ያደረጉ ባለሙያ ነበሩ።
ጋዜጠኛ ነጋሽ ገብረማርያም ኤዲቶሪያል የሚለውን ርእስ አንቀጽ በሚል ከሌሎች ጋር ተማክረው የቀየሩት እሳቸው እንደነበሩም ይነገራል።