የካቲት ፮(ስድስት) ቀን፳፻፯ዓ/ም ኢሳት ዜና :-መንግስት ባለፈው የክረምት ወር ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሰጠውን የፖለቲካ ስልጠና ለከምባ ወረዳ የመንግስት ሰራተኞች ሲሰጥ ቢቆይም፣ ሰራተኞች ለጠየቅናቸው ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ አልተሰጠንም በሚል ፣ በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ አስተያየት አንስጠም በማለታቸው ስብሰባው መተናቀቁን በስብሰባው የተገኙ ተስብሳቢዎች ተናግረዋል።
“በደቡብና በጋምቤላ ክልሎች መካከል ያለው የእርሻ ቦታ ለኢህአዴግ አባላት ኢንቨስተሮች ለምን ተሰጠ? ኢትዮጵያ እየተበደረቸው ያለው ገንዘብ መጪውን ትውልድ በእዳ ጫና እንዲጎዳ የሚያደርግ አይደለም ወይ? ሰላማዊ ሰልፍ የሚወጡ ዜጎች ለምን በጥይት ይመታሉ? የሚሉና ሌሎችም በርካታ ጥያቄዎች በመንግስት ሰራተኞች ቀርቧል። ካድሬዎቹ ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ አለመስጠታቸው ያበሳጫቸው የመንግስት ሰራተኞች፣ በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ ምንም አይነት አስተያየት አንሰጥም በማለታቸው ውይይቱ በተቀውሞ ተጠናቋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በደረሶና በካምባ ወረዳዎች መካከል፣ ኮሻሌ በሚባል ቀበሌ አንድ አርሶ አደር ከ6 ያላነሱ የገዢው ፓርቲ ደጋፊዎችን ገድሏል፡፡ አርሶአደሩ እርምጃውን የወሰደው ለረጅም አመታት ይጠቀምበትን የነበረውን መሬት፣ በኢህአዴግ ባለስልጣናት ተቀምቶ ለኢንቨስተር በመሰጠቱ ነው። አርሶ አደሩን ለመያዝ የፌደራል ፖሊስ አባላት ቢሰማሩም፣ እስካሁን ሊይዙት እንዳልቻሉ የአካባቢው ምንጮች ገልጸዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የከምባ ወረዳ ባለስልጣናትን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።