የካቲት ፲፯ ( አሥራ ሰባት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአማራ ክልል በተደጋጋሚ በሚደረገው የመከላከያ ሰራዊት ምልመላ ያልተሳካላቸው የጦር ኃይሉ የቅጥር ቡድን፣ በመሰናዶና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚያደርጉትን የወታደር ምልመላ ቅስቀሳ ሊያቆሙ እንደሚገባ መምህራን ጠይቀዋል፡፡
በተለይ በባህር ዳር ከተማ መሰናዶ ትምህርት ቤቶች በመማር ላይ ያሉ ተማሪዎችን ሆን ብሎ ለመቀስቀስ በትምህርት ቤቱ የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ የቅጥር ማስታወቂያውን በመለጠፍ ተማሪዎች በትምህርታቸው ላይ ትኩረት እንዳያደርጉ በተዳጋጋሚ መሞከሩ አግባብ እንዳልሆነ መምህራኑ ተናግረዋል፡፡
የምልመላ ቡድኑ ለመከላከያ ሰራዊት አባልነት ለመቅጠር ያወጣው ተደጋጋሚ ማስታወቂያ ምንም አይነት ምላሽ በማጣቱ በወታደራዊ ኢንጅነርነት ስም በማታለል በኢሮውቲካል፣ኤሌክትሪካል፣ኤሌክትሮኒክስ ኢንጂነሪንግ እና ኮምፒዩተር ኢንፎርሜሽን የትምህርት መስክ ቅጥር ለመፈጸም ለተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ያወጣው ማስታወቂያም ውጤት አልባ ሆኖበታል፡፡
በዚህ ተስፋ ያልቆረጠው አገዛዙ ወጣቶችን ለጸረ ሽብርና አድማ በታኝ ፖሊስ አባልነት እንዲመዘገቡ ከአራተኛ ክፍል በላይ ላሉ ተማሪዎች ያቀረበው ጥሪም በቂ ምላሽ አለማግኘቱን የክልሉ ወኪላችን ገልጻለች።