ገዢው ፓርቲ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እያደረሰ ያለውን ጥፋት የሚያወግዙ የተቃውሞ ሰልፎች ተደረጉ

ጥር ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በተለያዩ የኦሮምያ አካባቢዎች እና በሰሜን ጎንደር የገዢው ፓርቲ ታጣቂዎች በህዝቡ ላይ ያደረሱትን እልቂት የሚያወግዝ፣ በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች፣ ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች እንዲፈቱ የሚጠይቅ እንዲሁም ከሱዳን ጋር በመሬት ዙሪያ የሚደረገው ድርድር እንዲቆም የሚጠይቁ የተቃውሞ ሰልፎች በአውሮፓ ህብረት መቀመጫና ብራሰልስ እና በሙኒክ ጀርመን ተካሂደዋል።
ከተለያዩ አጎራባች ከተሞች የተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን በአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ጽ/ቤት ፊት ለፊት በመገኘት ገዢውን ፓርቲ የተለያዩ መፈክሮችን በማሰማት አውግዘዋል። ህብረቱ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድም ጠይቀዋል።
በሙኒክ ከተማ በተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ደግሞ ኢትዮጵያውያኑ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በመገኘት ተቃውሞአቸውን ከማሰማታቸው በተጨማሪ የተለያዩ ጥያቄዎችን የያዙት ደብዳቤ አስገብተዋል። በእንግሊዝ ኢምባሲ በኩል በማለፍ ደግሞ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ይፈታ የሚሉ ጥያቄዎችን አሰምተዋል። በአሜሪካ ኢምባሲም በመገኘት አሜሪካ ለኢህአዴግ አገዛዝ የምታደርገውን ድጋፍ እንድታቆም መጠየቃቸውን በስፍራው የተገኘው ሃይሉ ማሞ ገልጿል።
በክልሉ አሁንም ከፍተኛ ውጥረት ያለ ሲሆን ዜጎች በገፍ እየታሰሩ ነው።
የአውሮፓ ህብረት በኦሮምያ እና በአማራ ክልሎች የተፈጸሙ ግድያዎችን በተመለከተ የተለያዩ ጥያቄዎችን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቴድሮስ አድሃኖም ማቅረቡን ለማወቅ ተችሎአል። ከውይይቱ በሁዋላ የህብረቱ ተወካይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በጋራ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም ፣ ዝግጅቱ እንዲሰረዝ ተደርጓል። ለምን እንደተሰረዘ ግን እስካሁን በይፋ የታወቀ ነገር የለም።