ጥር ፭ (አምስት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- አገዛዙ በመላ አገሪቱ የሚታየውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ህዝብን ያረጋጋልኝ ይሆናል በማለት በሚያደርጋቸው ስብሰባዎች ላይ ከፍተኛ ውግዝት ማስተናገዱን ቀጥሎአል።
በከተማ ልማትና ቤት ሚ/ር ከሰኞ ታህሳስ 23 እስከ ዓርብ ታህሳስ 28/ 2009 ዓ.ም. በተደረገው የ5 ቀናት የጥልቅ ተሃድሶ ውይይት በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ማለቅ ባለመቻሉ ተጨማሪ ሁለት ቀናት ወስዶ ባለፈው ማክሰኞ ተጠናቋል፡፡
ሠራተኞቹ በውይይቱ ማሃል ‹‹ ከህዝቡና ከእናንተም በየመድረኩ የምንሰማው ገዢው ፓርቲ የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ ችግር እንደገጠመው ነው፡፡ እኛም በሥራችን የምንረዳው ይህንኑ ነው፡፡ የህዝብም የእኛም አረዳድ ይህ በሆነበት ፣እናንተም መታደስ ብቻ ሳይሆን በጥልቅ መታደስ አለብን ባላችሁበት ፣ የምትነግሩን የመንግስት ገድል፣ የምታበስሩን የልማታዊ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ስኬት ከወዴት የተገኘ ነው? ወይስ ለእኛ የማይታይ ለእናንተ ብቻ የተከሰተ ‹ህዝቡ እንደሚለው ለብቻችሁ ጥቅም የዋለውን ዕድገትና ልማት ነው የምትነግሩን ?› ይህ ከሆነ ስብሰባው አያስፈልግም፤25 ዓመት ሲነገረን ቆይቷልና በከንቱ የግልና የመንግስት የስራ ሰዓት አናባክን፡፡ በግልጽ እንነጋገር ከተባለ እንደድርጅትም እንደ መንግስትም የቀረበላችሁ የህዝቡ ጥያቄ ‹አገሪቱን መምራት አልቻላችሁም፣ የምትሉት ዕድገትና ልማት ከእናንተ አልፎ ለእኛ አልደረሰንም፣ዘላቂና ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋል፤› ነውና በዚህ መንስኤና መፍትሄ ላይ እንነጋገር፤ ያለበለዚያ ከንቱ ድካም ነው፡፡›› በማለት የቀረበው ሃሳብ መልስ ሳያገኝ ውይይቱ እእንዲቀጥል ተደርጓል፡፡
ሰራተኞች አያይዘውም‹‹ ከመሥሪያ ቤታችን የሚወጡ በእውነት ላይ ያልተመሰረቱ ሪፖርቶች ከግምት የሚጥሉን ናቸው፡፡ ከእኛ ሪፖርት ከተደረገው 88 ኮንዶሚኒየም ጠፍቷል። ማለትም አልተሰራም ፡፡ይህ እየሆነ ባለበት ህዝቡን በተሳሳተ መረጃ የቤት ባለቤት፣ ወጣቱን የሥራ ባለቤት አድርገናል ማለት በእጅጉ አሳዛኝ ነው፡፡ ግን ለዚህ ዝርክርክ አሰራርና የህዝብና የአገር ሃብት ውድመት ሚኒስትሩ ከሥልጣናቸው ቢወርዱም እርሳቸውም ሆነ ሌላ ማንም አመራር ተጠያቂ ያለመሆኑ አስተዛዛቢ ነው፡፡ “ ብለዋል።
መድረኩ በአንድ በኩል ስለግልጽነት እየተሰበከበት በሌላ በኩል ሠራተኛውን የማስፈራራትና የአመራሩን አይነኬነትና ለማረጋገጥ የቀደመውን የተለመደ አሰራር ለማስቀጠል በሚደረግ ሙከራ የጥልቅ ተሃድሶውን ነገር ‹እንዳያማህ ጥራው፣ እንዳይበላ ግፋው› አድርጎታል ሲሉ ሰራተኞች ገልጸዋል። ሠራተኛው በገዢው ፓርቲና በመንግስት አመራር፣ ፖሊሲና አሰራር ላይ የሚያቀርበው ትችት እየበረታና እየጠነከረ ሲሄድ ከሁለተኛው ቀን በኋላ ዓላማውና አጀንዳው ወደ ‹ ግለሰቦች ግምገማ› እንዲቀየር ተደርጓል፡፡
በዚህ መድረክም ቢሆን አመራሮች የየራሳቸውን ክሊክ /ቡድን በመፍጠር እከክልኝ ሊከክልኝ በሚል እርስበርስ ሲሸፋፈኑ ተስተውሏል፡፡ በሚኒስትር መ/ቤቱ የኮሚኒኬሽን ሃላፊ ተዘጋጅቶ ጠቅላላ ሰራተኛው በጥልቅ ተሃድሶው የደረሰበት አቋም ነው በሚል የወጣውን መግለጫም ሰራተኞች ተችተውታል። ‹‹ ሰራተኛው ተወካይ ባልሰጠንበት፣ ስለአቋም መግለጫ ተነስቶ ባልተነጋገርንበት ፣ በማን እንደተዘጋጀ የማናውቀው የአቋም መግለጫ እኛን አይመለከተንም የሚል ሃሳብ ቢቀርብም ‹ጆሮ ዳባ ልበስ› ተብሎ በአንድ የአስተዳደር / ድጋፍ ሰጪ ሠራተኛ በሠራተኛው ሥም ተነቧል፡፡
በሌላ በኩል በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለከተማ ባሉ ወረዳዎች ሠራተኞች በጥልቁ ተሃድሶ አጀንዳ ላይ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ በሁሉም ወረዳዎች እየተነሱ ያሉት የሰራተኛው አስተያየቶች በምክር የተደረጉ የሚመስል ድባብ የተላበሱ ተመሳሳይ ናቸው፡፡
ሠራተኞች ‹‹ የሚከፈለን ደመወዝ እንዴት ሊያኖረን እንደሚችል የኑሮ ውድነቱ ፈተና በሆነብን ወቅት እናንተ የምታወሩት ጥልቅ ተሃድሶ ለእኛ ትርጉም አይሰጠንም፡፡ የምትነግሩን ዕድገትና ልማት በእኛ ኑሮ ላይ ያሳየው ለውጥ ቢኖር ከቀን ወደቀን በደመወዛችን እንኳን መሻሻል ከእጅ ወደአፍ ለሆነ ኑሮ አልበቃንም፡፡ ለእኛ ዘይት፣ ስኳር ማግኘት ባልቻልንበት ልማታችንና ዕድገታችን ለማስቀጠል የሚለው አይገባንም፡፡ ይህን ያመጡብን እነማን እንደሆኑ አይጠፋችሁም፣ ታውቃላችሁ፤ ዛሬ በወረዳና ክፍለከተሞች በር በዘመናዊ መኪና እየፈሰሱ የሚርመሰመሱት ጉዳይ አስፈጻሚዎችና ጉቦ አቀባባዮች የትናንት የየቢሮዎቹ ዘራፊ ሠራተኞች አይደሉም፣ አታውቋቸውምን? ግን ለፖለቲካውና ለራሳችሁ ጥቅም ስትሉ በተጠያቂነት አታውቋቸውም፣‹ በሥራ › ግን ከእኛ ባልደረቦቻችሁ ይልቅ ለእነርሱ ክብር ትሰጣላችሁ፣ ከህዝቡ በላይና በፊት የሚስተናገዱት እነርሱ ናቸው ፡፡ የሚሉ አስተያየቶችን አቅርበዋል።
“የምትሉትን ጥልቅ ተሃድሶ ከልብ ካሰባችሁበት ለመለወጥ የሚያስፈልገው መረጃና ማስረጃ በግልጽ የሚታወቅ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ኮንደሚኒዬም ጠፋ በሚባልበት ከተማ ፣ይህ በተወካዮች ም/ቤት በተነገረበት አገር እኛ ምን እንድንነግራችሁ፣ ምን እንድናደርግ ነው የምትጨቀጭቁን ? እባካችሁ እየተዋወቅን ስለምን እንወሻሻለን፤ እኛን ተዉን ›› በማለት በታከተ የተስፋ መቁረጥ ስሜት አስተያየታቸውን ያቀረቡ የመስተዳድሩ ሰራተኞች መኖራቸውን ወኪላችን ገልጿል።
በአዲስ አበባ ልደታ ክፍለ ከተማ በተደረገው የህዝብ መድረክ ላይ ነዋሪዎች ‹‹ ለማን ስንት እየከፈላችሁ እንደሆነ የምታውቁት እናንተ ናችሁ፡፡ 1500 ብር የምትከፍሉት ሠራተኛ በዘመናዊ መኪና ሥራ ሲመጣ ከየት አምጥቶ ነው አይባልም ? በአሁኑ ጊዜ የሚከፈለው ደመወዝ በአንድና ሁለት ዓመት ሙሉው ቢጠራቀም መኪና ይገዛል ? የአደባባዩን እውነት እናንተ ካልነገራችሁን በሚል ለምን ታደክሙናላችሁ ? ሁሉም ሚፈጸመው ከዓይናችሁ ሥር በግልጽ ነው ፤እንኳን እናንተ ማንም በአደባባይ የሚያየው ፣ ይሉኝታና ዕፍረት የሌለበት፣ እንዲያውም ሌብነትና ዝርፊያ የሚያኩራራና የሚያስከብር የሆነበት፤ በጎ ምግባር ፣ የሥነምግባር እሴቶች የተቀበሩበት፣ ማሾፊያ የሆኑበት፡፡ ታዲያ እኛን ምን አድርጉ ነው የምትሉን ፣ ልባችሁ እያወቀ በተራበ አንጀታችን ለምን በከንቱ ታደክሙናላችሁ?›› ገልጸው ነበር።