ጳጉሜን ፬(አራት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ የኢህአዴግን
ፖሊሲዎች ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ ለዳኞችና አቃቢያን ህጎች፣ ለፖሊሶች እንዲሁም
ለኢህአዴግ የተለያዩ ፎረም አባላት ሲሰጥ የቆየውን ስልጠና ለመንግስት ሰራተኛው
በሙሉ ለመስጠት ማቀዱ ታውቋል።
እስካሁን ድረስ በተካሄዱት ስልጠናዎች ኢህአዴግ ከአባላቱ ጭምር ሳይቀር ከፍተኛ
የጥያቄ ናዳዎችን ሲያስተናግድ የቆየ ቢሆንም፣ ውይይቱን ከማቋረጥ ይልቅ ወደ መንግስት
ሰራተኛው በማውረድ አስፋፍቶ ለመስጠት ማቀዱን ምንጮች ገልጸዋል።
በተለያዩ የማሰልጠኛ ጣቢዎች በሚሰጡት ስልጠናዎች ህዝቡ በአስተዳደሩ ላይ ያለውን
ምሬት፣ በአገሪቱ አካሄድ ደስተኛ አለመሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል። ኢህአዴግ መሰረታዊ
ችግሮቼ የአፈጸጻም እንጅ የፖሊሲ አይደለም በማለት ተሰብሳቢዎችን ለማሳመን ጥረት
አድርጓል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሁለተኛው ዙር የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የፖለቲካ ስልጠና ከመስከረም
5 ቀን ጀምሮ ለተከታታይ 18 ቀናት እንደሚሰጥ ለማወቅ ተችሎአል።
ስልጠናው የሚሰጠው ለአንደኛ አመት ተማሪዎች እና በልዩ ልዩ ምክንያቶች ላልተሳተፉ
ተማሪዎች ሲሆን፣ ስልጠናውን ያልተሳተፈ ተማሪ በአዲሱ የትምህርት ዘመን ትምህርት
ለመጀመር አይችልም።
ስልጠናው “ህገመንግስታዊ መርሆዎችና ሰላማያዊ የትግል ስልት እንዲሁም ልማታዊ
ዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታና ፈተናዎቹ፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች ትግልና አገራዊ ህዳሴያችን
እንዲሁም የተሃድሶ መስመርና የኢትዮጵያ ህዳሴ ” በሚሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደርጋል።
ኢህአዴግ የህዳሴ ጉዞአችን ከውጭና ከውስጥ ሃይሎች እየደረሰ ባለ ጥቃት ፈተና ውስጥ
መግባቱን ገልጾ፣ ህዝቡ ከኢህአዴግ ጎን ቆሞ እንዲታገላቸው ተማጽኖ ያቀርባል።
ገዢው ፓርቲ እስካሁን በተደረጉት ውይይቶች ለአበል እና ለተለያዩ ወጪዎች በመቶ
ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ማውጣቱን መዘገባችን ይታወሳል።