ገዢው መንግስት ተገቢውን ድጋፍና ክትትል ባለማድረጉ ለችግር መዳረጋቸውን ከአረብ ሃገር ተመላሾች ተናገሩ፡፡

ኀዳር ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በባህርዳር ከተማ ነዋሪ የሆኑ ወጣት ከስደት ተመላሾች ከዓመታት በፊት ወደ ሐገራቸው እንዲመለሱ በከፍተኛ የመንግስት አመራሮች በተደረገ ቅስቀሳ በመታለል ለረጅም ዓመት ያፈሩትን ሐብትና ንብረት በአግባቡ ሳይዙ ከተመለሱ በኋላ በማህበር ተደራጅተው ያለምንም ድጋፍና ክትትል በመተዋቸው ከፍተኛ ችግር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ወጣቶቹ የብድርና የመስሪያ ሸድ ተጠቃሚ ትሆናላችሁ ቢባሉም ፤ ከሁለት አመት በላይ ተሰርተው ያለ አገልግሎት የተቀመጡ በርካታ የመስሪያ ሸዶች እያሉ ወጣቶቹ እንዳይሰሩባቸው በመከልከላቸው በክራይ ቤት ለተጨማሪ ወጭ እየተዳረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ወጣቶቹ አክለው እንደተናገሩት የገዢው መንግስት የዜጎችን ወደ ሃገር ቤት መመለስ ለፖለቲካ ትርፍነት አዋለው እንጅ የገባውን ቃል በተግባር አለማዋሉ ያሳዘናቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በባህር ዳር ከተማ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሸዶች በህዳር አስራ አንድ እና ጣና ክፍለ ከተሞች ተዘጋጅተው ቢቀመጡም በሸዶች ውስጥ እየተጠቀሙ የሚገኙት በጣት የሚቆጠሩ ማህበራት በአመራሩ ዙሪያ የተሰባሰቡ ቤተሰቦች እንጅ አንድም ከስደት ተመላሽ ቦታው እንዳልተሰጠው ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል፡፡
የባህርዳር ጥቃቅን ፣ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ ወደ ስራ ሸዱ በመግባት ለመስራት የሚችሉ ቅድሚያ ከአረብ ሀገር ተመላሾች በመሆናቸው በማህበር በመደራጀት የመስሪያ ዕቃ እንዲያሟሉ እንዳደረጉ የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎች፤ የሚጠይቁትን ካሟሉ በኋላ እናንተ ራሳችሁን ችላችሁ መስራት ስለምትችሉ የመስሪያ ሸዱ አያስፈልጋችሁም በማለት መልሰው በመከልከል በክራይ ቤት እንዲንገለቱ ለሶስት ዓመታት መተዋቸውን ተናግረዋል፡፡
የመስሪያ ቦታው ለምን አይሰጠንም በማለት በተደጋጋሚ ለጠየቁት ተመላሾች መምሪያው የተሰጣቸው ምላሽ አዲስ ሃሳብ መሆኑን የሚናገሩት ወጣቶች፣ መምሪያው ‹‹ንግድ ፈቃድ አውጥቶ የመስሪያ ቦታ በማጣት ስራ ላልጀመረ ማህበር ነው የምንሰጠው ›› ማለቱ እንዳስገረማቸው ገልጸዋል፡፡
ተመላሾች እንደሚናገሩት አንድ ንግድ ፈቃድ ለማውጣት ከሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ የቤት ክራይ ውል ሲሆን ‹‹ የቤት ክራይ ውል ካልቀረበ ንግድ ፍቃድ አንሰጥም !! ›› በማለት ራሳቸው ያወጡትን ህግ እየጣሱት መሆኑ እጅግ ያሳዝናል በማለት ይናገራሉ፡፡
መምሪያው በፊት የገባውን ቃል በመርሳት ምንም አይነት የስልጠናም ሆነ የዕለት ከዕለት ክትትል ባለማድረጉ ገቢዎች ‹‹ የሂሳብ መዝገብ በአግባቡ አልያዛችሁም!›› በሚል ሰበብ ከፍተኛ ግብርና መቀጫ በመጣሉ ስራውን ለማቆም ተገደናል በማለት በምሬት የሚናገሩት ከስደት ተመላሾች በሃገራችንም ሰርተን ለመኖር የሚያስችለንን ዕድል እንዳንጠቀም ከፍተኛ ጫና በየአቅጣጫው እየተጣለብን ነው በማለት በምሬት ተናግረዋል፡፡

የገዢው መንግስት ከአረብ ሃገራት በየጊዜው ወጣቶችን ልዩ ልዩ ስልጠና ሰጠሁ፣አደራጅቸ ወደ ስራ አስገባሁ ቢልም፣ በስደተኞች ስም እየተጠቀሙ ያሉት የአመራር ቤተሰቦችና ከየአካባቢው አመራሮች ጋር የሙስና ንክኪ ያላቸው ማህበራት ብቻ መሆናቸውን ከስደት ተመላሾች ተናግረዋል፡፡