(ኢሳት ዲሲ–ጥር 14/2010)
ታዋቂው የእግር ኳስ ተጫዋች ጆርጅ ዊሃ ዛሬ የላይቤሪያን የመሪነት መንበር ተረከበ።
በሞኖሮቪያ ሳሙኤል ዶ ስታዲየም በተካሄደው ደማቅ ስነስርዓት የላይቤሪያን የፕሬዝዳንትነት ስልጣን የተረከበው ጆርጅ ዊሃ ለተሰበሰበው ሕዝብ ባደርገው ንግግር ብቻዬን የማደርገው ነገር የለምና አግዙኝ አብራችሁኝ ሁኑ ሲል ጥሪ አቅርቧል።
ላለፉት 12 አመታት በላይቤሪያ የመሪነት ስልጣን ላይ የቆዩትን ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍን ተክቶ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት በመሆን ዛሬ ቃለ መሃላ በመፈጸም የላይቤሪያን የፕሬዝዳንትነት ስልጣን የተረከበው ጆርጅ ዊሃ የላይቤሪያውያንን ፍላጎት ለማሟላት ቃል ገብቷል፡፡
ላይቤሪያውያንም እንዲያግዙት ጥሪ አቅርቧል።
የቃለ መሃላ ስነ ስርአት በርዕሰ መዲናዋ ሞኖሮቪያ ሳሙኤል ዶ ስታዲየም 35 ሺ ያህል ህዝብ በተገኘበት እጅግ ደማቅ በሆነ ስነስርአት ተካሂዷል።
የላይቤሪያ 25ኛ ፕሬዝዳንት በመሆን መንበረ ስልጣኑን የተረከበው ጆርጅ ዊሃ በአውሮፓ የእግር ኳስ ክለቦች ውስጥ የተጫወተ ዝነኛ የእግር ኳስ ተጫዋች እንደነበርም ይታወቃል።
የዊሊያም ሪቻርድ ቶልበርት መንግስት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1980 በመጋቢ ሃምሳ አለቃ ሳሙኤል ዶ ከተገለበጠበት ጊዜ ጀምሮ በቀውስ ውስጥ የቆየችው ላይቤሪያ በአማጺው መሪ ቻርለስ ቴይለርም ሰላም እንደራቃት ዘልቃልች።
ኢኮኖሚስቷና የመጀመሪያዋ እንስት የአፍሪካ መሪ ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ ከ10 አመት በፊት የመሪነቱን መንበር በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሲረከቡ ወደ ሀዲዱ የተመለሰው የላይቤሪያ ዲሞክራሲ ዝነኛውን የእግር ኳስ ተጫዋች ጆርጅ ዊሃን በፕሬዝዳንትነቱ ስልጣን ላይ በማስቀመጥ ቀጥሏል።
በዊሊያም ቶልበርት መንግስት ውስጥ ሚኒስትር የነበሩትና ከግድያ አምልጠው በሕይወት ከተረፉት ሚኒስትሮች አንዷ የነበሩት ኤለን ጆንሰን ሰር ሊፍ የላይቤሪያውያንን ሕይወት በመለወጥ ረገድ ያልተሳካላቸው ወይንም ውጤታማ ያልሆኑ መሪ መሆናቸውም ታውቋል።
ዛሬ የላይቤሪያን የፕሬዝዳንትነት መንበር የተረከበው የ51 አመቱ ጆርጅ ዊሃ “ብቻዬን የማደርገው የለምና አግዙኝ”ሲል ለላይቤሪያውያን ጥሪውን አቅርቧል።
“ፍላጎታችሁን ለማሳካት የምችለውን አደርጋለሁ” ሲልም ቃል ገብቷል።
ለሚቀጥሉት 6 አመታት የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ሆኖ የሚቀጥለው ጅርጅ ዊሃ በአመት 90 ሺ የአሜሪካን ዶላር ደሞዝ ተመድቦለታል።
ከ6 አመት በኋላ በድጋሚ ምርጫ ለመወዳደር መሳተፍ የሚችል ቢሆንም ለሶስተኛ ዙር እንዳይወዳደር የላይቤሪያ ሕገ መንግስት ይከለክላል።