ኢሳት (ጥር 11 ፥ 2008)
የጎረቤት ጅቡቲ መንግስት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ዕቃዎች ላይ በዘመናዊ ማሽን ፍተሻን በማካሄድ በአንድ ኮንቴንይነር እስከ 35 ዶላር ለማስከፈል የያዘውን እቅድ በሁለቱ ሃገራት መካከል አለመግባባት መፍጠሩ ተገለጠ።
ጅቡቲ የወሰደችውን አቋም ተከትሎም በኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተቋቋመ ቡድን ከሃገሪቱ ጋር ድርድር እያካሄደ እንደሚገኝ ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ጅቡቲ አዲሱን መመሪያዋን ከተያዘው ወር ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ እቅድን ይዛ የነበረ ሲሆን እርምጃው በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ አካላት ገልጸዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተቋቋመው ቡድን ድርድሩን ከሳምንታት በፊት ቢጀምርም እስካሁን ድረስ የተደረሰ ስምምነት አለመኖሩም ታውቋል።
ወደብ አልባ የሆነችን ኢትዮጵያ አብዛኛው የውጭ ንግዷንና የገቢ ምርቶቿን በጎረቤት ጅቡቲ በኩል የምታካሄድ ሲሆን በአመት ወደ 1.4 ቢሊዮን ዶላ አካባቢ ገንዘብ ለአገልግሎት እንደምታወጣም ይነገራል።
ሁለቱ ሃገራት ትስስራቸውን ያጠናክራል የተባለ በርካታ ስምምነቶችን መፈራረማቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ለጅቡቲ በነጻ የውሃ አቅርቦትን ለማድረግ ስምምነት ማድረጓም መዘገቡ ይታወሳል።
ጅቡቲ በበኩሏ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ከወደብ አገልግሎት ጋር የተገናኙ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ እንደምታደርግ ስትገልጽ ቆይታለች።
ይሁንና ሃገሪቱ እንዲህ ያለ ክፍያን ተግባራዊ ለማድረግ እቅድ ማያዟ በሁለቱ ሃገራት መካከል አለመግባባት መፍጠሩ ተገልጿል።