(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 19/2011) የሰው ልጅ የስቃይ ማዕከል በሚል የሚታወቀው ጄይል ኦጋዴን እስር ቤት ለጎብኚዎች ክፍት መሆኑ ተገለጸ።
የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፋ መሀመድ ዑመር ለኢሳት እንደገለጹት በቀድሞ የክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ ዒሌ የተከፈተውና የፖለቲካ ተቀናቃኞች የሚሰቃዩበት፡ ቶርች የሚደረጉበትና የሚገደሉበት ጄይል ኦጋዴን በይፋ ከተዘጋ በኋላ ሙዚየም እንዲሆን ተደርጓል።
በሌላ በኩል አቶ ሙስጠፋ ኢትዮጵያዊነትን በሶማሌ ክልል ማጠናከር የቅድሚያ ተግባራቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ጎጠኝነት መጨረሻው የሀገር ጥፋት በመሆኑ በክልላቸው በጎሳዎች መሀል ያለውን አንድነት በማጠናከር በኢትዮጵያ ግንባታ ላይ የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውንም ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
የ49 ዓመቱ ጎልማሳ በጎሳ ውጥረትና ሙስና የተዳከመውን ክልል ቀና ለማድረግ አዲስ መንገድ መከተላቸው ይነገራል።
ከጠባቡ መንገድ ወጣ ብለው ሰፊውን ጎዳና ይዘው ወደ ዜግነት ፖለቲካ ለመድረስ ጉዞ ጀምረዋል።
አካሄዳቸው ከሁለት ወር በፊት የነበረውን የክልሉን አጠቃላይ ገጽታ ሊቀይረው የሚችል እንደሆነ እየተነገረላቸው ነው።
ስለኢትዮጵያዊነት በየሄዱበት፡ በየተጠሩበት መድረክ ሲናገሩ የሁላችን መውጪያና ማሸነፊያ መንገድ እሱ ብቻ ነው የሚለውን መቋጠሪያ ሀሳብ ሳይገልጹ አያልፉም። አቶ ሙስጠፋ መሀመድ ዑመር።
የሶማሌ ክልልን ከአብዲ ዒሌ ከተረከቡ ሁለተኛ ወራቸውን እያገባደዱ ነው።
እንደእሳቸው አባባል ክልሉ ከፍርሃትና ስጋት ተላቆ በተስፋ መንገድ ላይ ወጥቷል።
በተለያዩ መስኮች የነበሩት ውጥረቶች ረግበዋል። የጎሳ ግጭቶች ቀንሰዋል። እንደጀመርነው ከዘለቅን የህዝብን እምባ አብሰን በደሉን እንክሰዋለን ነው የሚሉት አቶ ሙስጠፋ።
ለተስፋ ጅምራቸው የሶማሌ ክልል ተወላጆች እንደሲዖል የሚቆጥሩትና በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ስቃይና መከራ የተቀበሉበትን ጄይል ኦጋዴንን ዘግተዋል።
አቶ ሙስጠፋ እንደሚሉት ጄይል ኦጋዴን ተዘግቶ ሙዚየም ሆኗል።
ህብረተሰቡ በፈለገው ጊዜ መጥቶ እንዲጎበኘው ክፍት ተደርጓል ብለዋል ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ።
በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊውና በፖለቲካ ረገድ የሶማሌ ክልል በሁለት ወር ውስጥ ያሳየው መልካም ለውጥ ጉልበት ሰጥቶናል የሚሉት አቶ ሙስጠፋ አልፎ አልፎ ከሚከሰት የጸጥታ ችግር በቀር በአንጻራዊ መልኩ ሰላምና መረጋጋት ሰፍኗል ይላሉ።
በህወሃት ዘመን በክልሉ የውሸት ኢትዮጵያዊነት ሲሰበክ ቆይቷል የሚሉት አቶ ሙስጠፋ ይህ ደግሞ ከኢትዮጵያዊነት በላይ የጎሳ ማንነት እንዲጠናከርና ለግጭት ምክንያት ሆኖ ቆይቷል ብለዋል።
የጎጠኝነት መጨረሻው ሀገር ማፍረስ እንደሆነ የገለጹት አቶ ሙስጠፋ በእሳቸው የስልጣን ዘመን በኢትዮጵያ ላይ አሻራቸውን የማኖርና እኩል ተሳታፊ የመሆን አቅም ለመገንባት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ የሚያደናቅፉ ሃይሎች አሁንም ችግር እየፈጠሩ እንደሆነም አቶ ሙስጠፋ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
ከሐምሌ 28 ጀምሮ በአብዲ ዒሌ ታጣቂዎችና ደጋፊዎች አማካኝነት በተወሰደ ርምጃ የተገደሉ ሰዎች የተቀበሩበት በርካታ የጅምላ መቃብሮች መገኘታቸውን የጠቀሱት አቶ ሙስጠፋ የሃገር ሽማግሌዎች የምርመራ ስራቸውን አጠናቀው ውጤቱን ለፌደራል መንግስት ለመላክ በዝግጅት ላይ ናቸው ብለዋል።
በአቶ አብዲ ዒሌ የተደራጀው ሄጎ የተባለ የወጣቶች ቡድን ሙሉ በሙሉ መፍረሱንም ገልጸዋል።
አቶ ሙስጠፋ በቅርቡ ወደ አማራ ክልል እንደሚያመሩም ነው ለኢሳት የገለጹት።