ጃፓን በደቡብ ሱዳን አሰማርታ የምትገኘውን የሰላም አስከባሪ ሃይል ለማስወጣት ወሰነች

ኢሳት (መጋቢት 1 ፥ 2009)

የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ በደቡብ ሱዳን ተሰማርተው የሚገኙ የጃፓን የሰላም አከባሪ ሃይሎች ከአንድ ወር በኋላ ጠቅልለው እንደሚወጡ መግልጻቸውን ቢቢሲ የጃፓኑን ዜና አገልግሎት (ኪዮዳን) ዋቢ በማድረግ ዘግቧል። ደቡብ ሱዳን ወደ አዲስ መንግስት ግንባታ በመሸጋገሯ ጃፓን በተለያዩ ዘርፎች ስትሰጥ ከቆየችው ድጋፍ ለመውጣት ወስናለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

የጃፓን ባለስልጣናት የተወሰደው ዕርምጃ እያሽቆለቆለ ከመጣው የደቡብ ሱዳን የጸጥታ ሁኔታ ጋር የተገኛኘ አይደለም ሲሉ አክለው ገልጸዋል።

በተያዘው ሳምንት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አዲሲቷን ሃገር ወደ ዘር ማጥፋት እያመራች ነው ሲል ስጋቱን ማስታውቁ የሚታወስ ሲሆን፣ በሃገሪቱ ያለው የረሃብ አደጋም በሰዎች ላይ ጉዳትን እያስከተለ እንደሆነ ይነገራል። ራስን የመከላከል ስልጣን የነበራቸው ከ350 በላይ የጃፓን ወታደሮች በደቡብ ሱዳን ከሰላም ማስከበሩ ጎን ለጎን በግንባታ ስራዎች ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደረጉ እንደነበር ታውቋል።

የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመጀመሪያ ጊዜ በደቡብ ሱዳን ያሰማሩት የሰላም አስከባሪ ሃይል አባላት ተከትሎ ከሃገራቸው የፓርላማ አባላት ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ ይቀርብባቸው እንደነበርም ለመረዳት ተችሏል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ አቤ አንድም የሰላም አስከባሪ ቢሞት ስልጥእናቸው በገዛ ፈቃዳቸው እንደሚለቁ ቃል ገብተው የነበረ ሲሆን፣ ለዚሁ ውሳኔያቸው የደቡብ ሱዳን የጸጥታ ሁኔታ ምክንያት መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች ገልጸዋል። ጃፓን የሰላም አስከባሪ ሃይሏን ብታስወጣም፣ ለሃገሪቱ የምትሰጠውን አለም አቀፍ ድጋፍ ግን ትቀጥላለች ሲሉ አቤ ተናግረዋል።

የደቡብ ሱዳን መንግስታትና በሪክ ማቻር የሚመራው አማጺ ቡድን የደረሱትን ስምምነት ተግባራዊ ሊሆን ባለመቻሉ ሃገሪቱ በግጭት ውስጥ መሆኗ እና ችግሩ ዘላቂ አለመረጋጋት ሊያመጣ እንደሚችል የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።

ሃገሪቱ ከጎረቤት ሱዳን ጋር በምትዋሰንበት የአብዬ ግዛት ከ6ሺ በላይ የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ሃይሎች የሚገኙ ሲሆን፣ ሁለቱ ጎረቤት ሃገራት በነዳጅ ሃብት የምትታወቀው ግዛት ላይ የባለቤትነት ጥያቄን አንስተው ይገኛሉ። በአካባቢው የሰላም አስከባሪ ሃይል ቢሰማራም፣ ደቡ ሱዳንና ሱዳን ጥያቄያቸው ዕልባት ማግኘት አልቻለም።