(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 7/2010)
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ የፈጸምኩት ምንም ጥፋት ስለሌለ ከስልጣን የምወርድበት ምክንያት የለም ሲሉ ለፓርቲያቸውም ምላሽ መስጠታቸው ታወቀ።
የደቡብ አፍሪካው ገዢ ፓርቲ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ጃኮብ ዙማ በሙስናና በልዩ ልዩ ተደራራቢ የወንጀል ክሶች ተጠያቂ በመሆናቸው ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው እንዲለቁ ግፊት ሲያደርግ ቆይቷል።
ነገር ግን ፕሬዝዳንቱ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ስልጣን እንደማይለቁ አረጋግጠዋል።
ፓርቲያቸው እያቀረበላቸው ያለው ጥያቄም ቢሆን ትክክል ያለሆነና አግባብነት የሌለው ነው ሲሉ ለሃገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ፓርቲያቸው ከስልጣን እንዲለቁ ያቀረበላቸውን ጥያቄም ቢሆን አልቀበልም ማለታቸውን ቢቢሲ በዘገባው ላይ አስፍሯል።