ዶ/ር አብይ አህመድ በሶማሌው ርዕሰ መስተዳድር በአቶ አብዲ ኢሌ ላይ ምርመራ እንዲካሄድ ትዕዛዝ ይሰጡ ዘንድ ሂውማን ራይትስ ዎች ጠየቀ

ዶ/ር አብይ አህመድ በሶማሌው ርዕሰ መስተዳድር በአቶ አብዲ ኢሌ ላይ ምርመራ እንዲካሄድ ትዕዛዝ ይሰጡ ዘንድ ሂውማን ራይትስ ዎች ጠየቀ
(ኢሳት ዜና ሰኔ 28 ቀን 2010 ዓ/ም) ዓለማቀፉ የሰብአዊ መብት ድርጅት ባወጣው መግለጫ በክልሉ በሚገኘው የኦጋዴን እስር ቤት ውስጥ በተፈጸሙት አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ምርምራ ማካሄዱን በመጥቀስ፣ የደህንነት ሰራተኞችና ባለስልጣናት ተጠያቂ እንዲሆኑ ያደርጉ ዘንድ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠይቋል።
“የሞቱትን እንመስላለን” በሚል ርዕስ የተጻፈው ባለ 88 ገጽ የተቋሙ ሪፖርት በኦጋዴን እስር ቤት ውስጥ የተፈጸሙትን ሰቆቃዎች፣ አስገድዶ መድፈር እና ሌሎችንም የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በዝርዝር ያትታል። ለተፈጸሙት ወንጀሎች የእስር ቤት ባለስልጣናት እና የሶማሊ ልዩ ሃይል አባላት ተጠያቂዎች መሆናቸውን የገለጸው ሪፖርቱ፣ ልዩ ኃይሉም ለክልሉ ፕሬዚዳንት ለአቶ አብዲ ሙሃመድ ኡመር ተጠሪ መሆኑን ገልጿል።
አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የጸጥታ ሃይሎች በህዝብ ላይ ሰቆቃዎችን መጸፈማቸውን ቢያምኑም፣ ወንጀለኞችን ለፍርድ በማቅረብ በኩል የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ባህል እየሆነ የመጣውን ወንጀል የሰሩ ባለስልጣናትን ያለመጠየቅ ባህል እንዲሰብሩ ጠይቋል። በኦጋዴን እስር ቤት ውስጥ የሚፈጸሙ አሰቃቂ እርምጃዎች በፍጥነት ምርመራ እንዲካድባቸው ሲልም ሂውማን ራይትስ ዎች ጨምሮ አሣስቧል።
አንድ እስረኛ “ ለብቻዬ በጨለማ ውስጥ ለ3 ዓመታት ታሰርኩ። በሌሊት እየተወሰድኩ እደበደባለሁ። የዘር ፍሬዎቼን በኤሌክትሪክ ጠብሰዋቸዋል። እጄን ወደ ሁዋላ አዙረው በሽቦ አስረውኛል። በርበሬ የሞላበት ፕላሲቲክ በአናቴ ላይ አስቀምጠውብኛል።” ብሎአል።
ምንም ክስ ሳይመሰረትበት ለ5 አመታት በእስር የቆየው የ40 አመቱ ጎልማሳ ሆዳን በበኩሉ፣ በአጠቃላይ እስረኞች ፊት ራቁቱን አቁመው እንደገረፉት ገልጿል። አንድ ሽማግሌ ከሴት ልጃቸው ጋር እርቃናቸውን ሆነው በእስረኞች ፊት እንዲቆሙ መደረጋቸውንም ተናግረዋል።
ዋና የእስር ቤት ሃላፊዎችና የልዩ ፖሊስ አዛዦች በድብደባና በሌሎችም የማሰቃያ ዘዴዎች ከመሳተፋቸውም በተጨማሪ በአስገድዶ መድፈር ውስጥ እጃቸው እንዳለበት እስረኞች ገልጸዋል።
በኦጋዴን እስር ቤት ውስጥ በዘበኞች ተደፍረው የወለዱ ሴቶች፣ የደረሰባቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰትም አጋልጠዋል።
የሂውማን ራይትስ ወች የአፍሪካ ተመራማሪ ፊሊክስ ሆርን ፣ በኦጋዴን እስር ቤት የተፈጸመው ግፍ የተጋነነ አለመሆኑን ገልጸዋል። ዶ/ር አብይ በኦጋዴን እስር ቤት ውስጥ አሰቃቂ የማሰቃያ ድርጊቶችን በፈጸሙት ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ፊሊክስ ሆርን ጠይቀዋል።