ዶ/ር አብይ ለፍትህ፣ ለነጻነትና ለእውነተኛ ዲሞክራሲ እንዲሰሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አሳሰቡ
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 12 ቀን 2010 ዓ/ም) የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጎንደር ከተማ የተገኙትን አዲሱን ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ለመቀበል በተዘጋጀ ስነስርዓት ላይ እንደተናገሩት፣ የአማራ ህዝብ በተለይም የክልሉ ህዝብ የዶ/ር አብይን የጠ/ሚኒስትርነት ስልጣን በደስታ የተቀበለው፣ ህዝቡ ለውጥ በመፈለጉና እርሳቸውም የለውጥ ምልክትና ተስፋ ተደርገው በመቆጠራቸው ነው።
ዶ/ር አብይ እስካሁን ያስተላለፉዋቸው መልዕክቶች ተራማጅ ናቸው ያሉት አቶ ገዱ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ የናፈቀውን የለውጥ ፍላጎት ማንጸባረቃቸው ድጋፍ እንዲያገኙ እንዳደረጋቸው ገለጸዋል። “ ህዝቡ ድጋፍ እየሰጠዎት ያለው በለውጥ ፈላጊነትዎ ምክንያት መሆኑን ላሰምርልዎት እፈልጋለሁ” ያሉት አቶ ገዱ፣ የሚፈለገውንም ለውጥ ሲያስረዱ፣ “ በአገራችን ኢትዮጵያ ከዳር ዳር ሁሉም ህዝቦች ያለስጋትና መሸማቀቅ በነጻነት የሚኖሩበት፣ ለዜጎች የሚሰጠው አገልግሎት ግልጽነትና ፍትሃዊነት የሰፈነበት እንዲሆን፣ የአብሮነት እሴት ተጠብቆ በጽኑ አንድነትና ፍቅር መኖር” ነው ብለዋል።
መሪ ድርጅቱ ኢህአዴግና መንግስታዊ መዋቅሩ ለለውጥ አደናቃፊ ሳይሆን የለውጥ ሞተር መሆን አለበት ያሉት አቶ ገዱ፣ የጎንደር ህዝብ አዲሱን ጠ/ሚኒስትር አክብሮ የተቀበላቸው የለውጥ ፍላጎት ስላለው መሆኑን ገልጸዋል።
“የጎንደር ህዝብ ከጥንት እስከ ዛሬ ለፍትህ መስዋዕትነት እየከፈለ የመጣ ህዝብ ነው ። ለፍትህ ሺዎችን የገበረ ህዝብ ነው ። አሁንም እርስዎ በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህና ነፃነትን ለማስፈን በሚያደርጉት ትግል የጎንደር ህዝብ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል የማያቅማማ መሆኑን ስገልጽልዎት፣ በሙሉ እምነት በታላቅ ኢትዮጵያዊ አክብሮትና ኩራትም ጭምር ነው ፡፡” ሲሉ ኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛ ነጻነትና ፍትህ መምጣት እንዳለበት ገለጸዋል።
አቶ ገዱ በአዲሱ ጠ/ሚኒስትር መሪነት በኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛ የዲሞክራሲ ስርዓት እንዲሰፍን፣ የህዝቡ ፍቅርና አንድነት እንዲጎለብት፣ፍትህ እንዲሰፍን፣ ድህነት እና ሁላ ቀርነት እንዲጠፋ ምኞታቸውን ገልጸዋል።
አቶ ገዱ በንግግራቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ነጻነት አለመስፈኑን፣ ፍትሃዊ ስርዓት አለመመስረቱን፣ ማህበራዊ እኩልነት አለመኖሩን እንዲሁም በአገሪቱ እውነተኛ ዲሞክራሲ የሌለ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው መግለጻቸው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህና ነጻነት መስፈኑን በየጊዜው ከሚናገረው ብአዴን የተለዬ እይታ እንዳላቸው የሚያመላክት ነው ተብሏል።
ዶ/ር አብይ ለህዝቡ ባደረጉት ንግግር የጎንደር ህዝብ ለኢትዮጵያ አንድነት በከፈለው መስዋትነት አድናቆታቸውን ገልጸዋል። “ ጎንደር የድንቅ ታሪክ ባለቤት-የዘመነዊቷ ኢትዮጵያ ጽኑ መሰረት- የጥበብ እና ውበትም ቤት- የእምነት እና የድል ተምሳሌት ናት፡፡ ጎንደር የተስፋ ጎህ ብስራት መፍለቂያ፤ የአንድነት ጸሀይ መፈንጠቂያ ተደርጎ ይታያል፡፡ በጦር አበጋዞች ፉክክርና የእርስ በርስ ጦርነት ሀገራዊ ህልውና አደጋ ላይ በወደቀበት በዚያ ዘመን ጎንደር የሀገራዊ አንድነት ትልም አመንጭታ የተስፋ ብርሃንን ፈንጥቃለች፡፡ አርማጭሆ የነ ራስ አሞራው ውብነህ ተሰማና ደጃዝማች ብሬ ዘገዬ፣ የነጻነት ተጋድሎና የአልበገር ባይነት ተምሳሌት ናት፡፡
ዛሬም የዚህ አደራ ተረካቢ ሆነን የሀገራችን ዲሞክራሲያዊ አንድነት በፍትህና በነጻነት መደላድል ላይ መስርተን እንደምናስቀጥል እተማመናለሁ፡፡” በማለት ዶ/ር አብይ ተናግረዋል።