ዶክተር ፍቅሩ ማሩ የሞቱት ታካሚዎች ቁጥር 20 ደርሷል አሉ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 30/2010)

በከፍተኛ ጥበቃ ስር ሆኜ የልብ ሕሙማንን እንዳክም ጠይቄ ስላልተፈቀደልኝ የሞቱት ታካሚዎች ቁጥር 20 ደርሷል ሲሉ በእስር ላይ የሚገኙት ዶክተር ፍቅሩ ማሩ ለፍርድ ቤት ገለጹ።

ከእስር ቤት ወደ ፍርድ ቤት በአቃቢ ሕግ ምስክር አለማቅረብ ምክንያት መመላለስ እንደመረራቸውም ታዋቂው የልብ ሃኪም ዶክተር ፍቅሩ ማሩ በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት በእስር ቤት እየደረሰባቸው ያለውን እንግልት ተናግረዋል።

አቃቢ ሕግ ምስክር ማቅረብ ሲያቅተው በችሎት ውስጥ በሞባይል ጌም ይጫወታል።

እኔ ግን ከእስር ቤት ተመልሼ የምጫወተው ከትኋንና ከአይጥ ጋር ነው ይላሉ ከስውዲን መጥተው ኢትዮጵያውያንን በማከም ላይ እያሉ ለእስር የተዳረጉት ዶክተር ፍቅሩ ማሩ።

በእስር ቤት ውስጥ ሰብአዊነት የሚባል ነገር የለም፣አቃቢ ሕግም እንደከብት እያስጎተተ ፍርድ ቤት በካቴና አስሮን ከመጣን በኋላ ምስክር አላመጣልኝም እያለ እያጉላላን ነው ሲሉም የልብ ሃኪሙ ይናገራሉ።

ዶክተር ፍቅሩ ማሩ ለፍርድ ቤቱ እንደገለጹት በከፍተኛ ጥበቃ ስር ሆነው የልብ ሕሙማንን ለማከም ጥያቄ አቅርበው አልተፈቀደላቸውም።

በዚሁም ሳቢያ መዳን እየቻሉ ሃኪም አጥተው የሞቱት ታካሚዎ ቁጥር 20 ደርሷል ነው ያሉት።

ዶክተር ፍቅሩ እንደሚሉት አንድ ቀን ብቻ በ15ኛ ወንጀል ችሎት ዳኛ ተፈቅዶላቸው አንድ ሰው ብቻ ከፍተኛ ጥበቃ ስር ሆነው ለማከም ችለዋል።

ከዚያ በኋላ ግን ሕሙማንን ለመርዳት እንዳልቻሉ ነው የተናገሩት።

ከታሰርኩ 4 አመት ከ8 ወር ሆኖኛል ያሉት ዶክተር ፍቅሩ አሁንስ መረረኝ ማርም ሲበዛ ይመራል ሲሉ ተናግረዋል።

አቃቢ ሕግ ምስክሮች አቀርባለሁ እያለ ባለማቅረቡ ከፍተኛ መጉላላት እንደደረሰባቸውም ነው የተናገሩት ።

እናም የምክክር ሂደቱ ታልፎ ብይን ይሰጥልኝ በሚል ለፍርድ ቤቱ በምሬት አቤቱታ አቅርበዋል።

ፍርድ ቤቱም ቀጠሮው የተያዘው ለጥር 3/2010 በመሆኑ በዚህ የመጨረሻ ቀጠሮ ብይን እሰጣለሁ ብሏል።