(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 21/2010)ዶክተር አብይ አህመድ የኢሕአዴግ ሊቀመንበርነትን ያገኙት በመራራና እልህ አስጨራሽ ትግል ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ለማ መገርሳ ገለጹ።
አቶ ለማ ኦ ቢ ኤን ከተባለው የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አዲሱ የኢሕአዴግ አመራር ዝም ብሎ የተገኘ ሳይሆን በጠንካራና ሰፊ ትግል ነው ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ኦህዴድ የፌደራል ስርአቱን የመምራት ዕድል በማግኘቱ ድርብ ሃላፊነት ተሰጥቶታል ነው ያሉት።
የኦህዴድ ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አህመድ በኢሕአዴግ ምክር የተመረጡበት ሂደት
እልህ አስረጫሽ እና በጠንካራ ስራ የተደረሰበት ነበር ሲሉም አቶ ለማ መገርሳ ገለጸዋል።
ዶክተር አብይ አህመድ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ሆነው እንዲመረጡ ብአዴን የራሱን አስተዋጽኦ ማድረጉን የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን መግለጻቸውም ይታወሳል።
አቶ ለማ መገርሳ ኦህዴድ ሃገር የመምራት ሃላፊነት ተሰጥቶታል ቢሉም የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ “አሸናፊው ግለሰብ ሳይሆን ድርጅቱ ነው” ማለታቸው ይታወሳል።
የሕወሃቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው ምርጫው የግለሰብ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በጋራ የምንመክርበት ነው ማለታቸው አይዘነጋም።
አቶ ለማ መገርሳ ቀጣዩ ጊዜ ፈታኝ እንደሚሆንና ለሕዝቡ የገባነውን ቃል ለመፈጸም መስዋዕትነት እንከፍላለን ማለታቸውንም ኦ ቢ ኤን ዘግቧል።