ዶክተር አምባቸው መኮንን የአመራር ለውጥ እንደሚደረግ ገለጹ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 5/2011)ለኢትዮጵያም ሆነ ለአማራ ክልል ተጨባጭ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የታመነበት የአመራር ለውጥ እንደሚደረግ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን ገለጹ፡፡

የማይመጥኑ አመራሮችን በአዳዲስ የመተካት ሥራው ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዶክተር አምባቸው መግለጻቸውን የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በደረ-ገጹ አስታወቋል፡፡

በአማራ ክልል በወረዳ፣ ዞንና ክልል ደረጃ እስከ 70 በመቶ የሚደርስ የአመራር ለውጥ ከዚህ ቀደም ተደርጎ ነበር የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን ገልጸዋል።

ይህም ሆኖ ግን የመተካካት ሥራው በጥናት ያልተደገፈ እና በመረጃ ላይ የተመሠረተ ባለመሆኑ የተፈለገውን ውጤት አለመምጣም ሲሉ ችግሩን አስረድተዋል።

ዶክተር አምባቸው እንዳሉት በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በተደረገ ሕዝባዊ ውይይት የአመራር መተካካቱ ውጤታማ ያልሆኑባቸው አካባቢዎች እንዳሉ ተረጋግጧል።

በተለይ በቂ ልምድ የሌላቸው አመራሮች በመኖራቸው ሠራተኞችን በደንብ ወደ ሥራ ያለማሠማራት ውስንነት አለ ነው ያሉት፡፡

እናም በተሻለ መልኩ በዕውቀት ላይ የተመሠረተና ለክልሉም ሆነ ለሀገሪቱ ተጨባጭ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የታመነበት የአመራር ለውጥ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ከለውጡ ወዲህ የመንግሥት የሥራ ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ መቀዛቀዝ እየታየበት መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ዶር አምባቸው በካቢኔቸውም ወስጥ የተወሰኑ ባለስልጣናትን በማንሳት ሕግን ለማስከበር እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።