(ኢሳት ዲሲ–ጥር 21/2010)
በቅርቡ ከወህኒ የወጡት ዶክተር መረራ ጉዲና በአምቦና በጊንጪ ከተሞች ከፍተኛ አቀባበል ተደረገላቸው።
በተለይ በአምቦ ስታዲየም በተካሄደው የአቀባበል ስለስርአት በመቶ ሺ የሚቆጠር ሕዝብ እንደታደመም ለማወቅ ተችሏል።
ወደ አምቦ ባደረጉት ጉዞ በሌሎች የምዕራብ ሸዋ ከተሞች በተለይም በጊንጪ ከፍተኛ አቀባበል የጠበቃቸውና በአምቦ ስታዲየም የጀግና አቀባበል የተደረገላቸው ዶክተር መረራ ጉዲና ለሕዝቡ በተለይም ለወጣቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ትግሉ እንደሚቀጥል ቃል የገቡት ዶክተር መረራ ጉዲና እስከ ፍጻሜው አብረን እንሁን ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር የሆኑት ዶክተር መረራ ጉዲና ባለፉት 27 አመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል።
በተለይም የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስን ከመሰረቱበት ከ1988 ጀምሮ ላለፉት 22 አመታት በፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች አንዱ መሆናቸውም ይታወቃል።
ዶክተር መረራ ጉዲና የንጉሱን ስርአት በኋላም የደርግን ስርአት በመቃወም በመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ መኢሶን ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል።
በደርግ ስርአት በፖለቲካ ተሳትፏቸው ሳቢያም ለ7 አመታት ታስረዋል።
ታላቅ ወንድማቸውም በኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ውስጥ ሲሳተፉ በደርግ መገደላቸውም ታውቋል።
ታዋቂው ፖለቲከኛ ዶክተር መረራ ጉዲና በፖለቲካ ተሳትፏቸው ሳቢያ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ እንደከለከላቸው ማስረጃ ጠቅሰው ማሳወቃቸው ይታወሳል።
ዩኒቨርስቲው ከመምህርነት በተጨማሪ ከተከራዩበትም ቤት እንዲወጡ አድርጓቸዋል።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ እንደገና ወደ ወህኒ መጋዛቸው ብዙዎችን አስቆጥቷል።
አሁን ደግሞ በግፍ ከታሰሩበት መፈታታቸውን ተከትሎ ሕዝባዊ ድጋፍና ከበሬታ እየጎረፈላቸው ይገኛል።