ዶክተር መረራ ጉዲና ከወህኒ ወጡ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 9/2010)

የኦፌኮ ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲና ዛሬ ከወህኒ ወጡ።

ከሳቸው ሌላ በፖለቲካ ምክንያት የታሰሩ ሌሎች ታዋቂ ሰዎች ግን አልተፈቱም።

ዶክተር መረራ እንዲፈቱ ተወስኖ ክሱ ከተቋረጠ በኋላ የመንግስት ቃል አቀባዩ ዶክተር ነገሬ ሌንጮ ትላንት በሰጡት መግልጫ የዶክተር መረራ ጉዲና ጉዳይ ውሳኔ የሚያገኘው በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ነው ማለታቸው ይታወሳል።

የህወሃት ንብረት የሆነው ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከልም በተመሳሳይ አይፈቱም የሚል ዘገባ እንዳቀረበም ታውቋል።

ሆኖም ዶክተር ነገሬ ሌንጮ መግለጫውን ከሰጡ በኋላ እንደገና ዶክተር መረራ እንዲፈቱ መወሰኑ ተመልክቷል።

የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሜቴ ለ17 ቀናት ያካሄደውን ግምገማ ተከትሎ ይፋ የሆነው እስረኞቹን የመልቀቅ ዜና ሲጓተት ቆይቶ ከዶክተር መረራ ጉዲና ውጪ ዋና ዋና የፖለቲካና የህሊና እስረኞችን ሳያካትት ዛሬ ተግባራዊ ሆኗል።

ክሳቸው ተቋርጦ ተለቀቁ ተብለው ከተገለጹት 115 ሰዎች ውስጥ አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ክሳቸው በሂደት ላይ የሚገኙ የኦፌኮ መሪዎችና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች አልተካተቱም።

የመንግስትና የፓርቲ መገናኛ ብዙሃን ዶክተር መረራ ጉዲናና ዶክተር ሩፋኤል ዲሳሳን ጨምሮ 115 ሰዎች ተፈቱ በማለት ሲገልጹ ሌላ የሚታወቅ ሰውን ግን መጥቀስ አልቻሉም።

እስረኞቹ የሚፈቱት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ነው ከሚለው ጋር የፍቺው ሂደት የሚጣጣም ሆኖ አለመገኘቱም አነጋጋሪ ሆኗል።

ታዋቂው ፖለቲከኛና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት የዶክተር መረራን መፈታት ቢቢሲን ጨምሮ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበውታል።

ከእስር ቤት ሲወጡም በደጋፊዎቻቸው ከፍተኛ አቀባበል እንደተደርገላቸውም ለማወቅ ተችሏል።

የዶክተር መረራን ፎቶግራፍ በካናቴራቸው ላይ ያሳተሙ ወጣቶችን ጨምሮ በርካታ ደጋፊዎቻቸው ዶክተር መረራን ወህኒ ቤት ድረስ ተገኝተው ተቀብለዋቸዋል።

መኖሪያ ሰፈራቸው ሲደርሱም ከፍተኛ አቀባበልና መስተንግዶ እንደተደረገላቸውም ታውቋል።

ዶክተር መረራ ጉዲና በኢትዮጵያ ጉዳይ በሚመክር ስብሰባ ላይ ለመገኘት በአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ግብዣ ብራስልስ ደርሰው ሲመለሱ መታሰራቸው ይታወሳል።

ዶክተር መረራ በህዳር 2009 የታሰሩ ሲሆን ከአንድ አመት ከሁለት ወር የእስር ቤት ስቃይ በኋላ ተፈተዋል።