ኢሳት(ጥር 16 ፥ 2009)
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ከግብፁ አቻቸው አብደልፈታህ አል ሲሲ ጋር ሽብርተኝነትን በጋራ ለመወጋት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን የአሜሪካ ባለስልጣናት ይፋ አደረጉ።
ስልጣናቸውን ከተረከቡ ከአራት ቀን በኋላ ከፕሬዚደንት አል ሲሲ ጋር የስልክ መልዕክት የተለዋወጡት ፕሬዚደንት ትራምፕ፥ ሃገራቸው ከግብፅ ጋር ሁለገብ ግንኙነት ለማጠናከር እንደምትፈልግ መግለጻቸውን ሮይተርስ ባለስልጣናት ዋቢ በማደረግ ዘግቧል።
የግብፅ ፕሬዚደንት በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ጉብኝት እንዲያደርጉ የጠየቁት የአሜሪካ ፕሬዚደንት ግብፅ ሽብርተኛነትን ለመዋጋት እያደረገች ያለውን ጥረት እንዳደነቁም የ White House ቃል አቀባይ ሲአን ስፓይሰር ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።
የፕሬዚደንት አልሲሲ ቃል አቀባይ የሆኑት አላ ዮሴፍ በበኩላቸው ሁለቱ መሪዎች ግብፅ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እያደረገች ያለውን ጥረት ለማገዝ ስምምነት መድረሳቸውን ለሮይተርስ አስታውቋል።
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ግብፅ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እያካሄደች ያለውን ጥረት ለማገዝ ወታደራዊ እገዛን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ ቃል መግባታቸውን የግብፅ ቃል አቀባይ አክለው አስረድተዋል።
ፕሬዚደንት ትራምፕ ግብፅ ላለችበት ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት ምን አይነት ድጋፍ መደረግ እንዳለበት ሃሳብ አንስተው መወያየታቸውንም የሁዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ለመገናኛ ብዙሃን አክለው ገልጸዋል።
የባራክ ኦባማ አስተዳደር ላለፉት በርካታ አመታት ኢትዮጵያን በሽብርተኛ ላይ በሚካሄዱ ጉዳዮች ዙሪያ እንደዋነኛ አጋር አድርጎ መቆየቱን የፖለቲካ ተንታኞች ሲገልጹ ቆይተዋል።
ይሁንና አዲስ የአሜሪካ መንግስት ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ከአፍሪካ ሃገራት መካከል ግብፅን በዋነኝነት መምረጡ የውጭ ፖሊሲ ላይ ለውጥ ሊኖር እንደሚችል ፍንጭ መሆኑን በመግለጽ ላይ ናቸው። አሜሪካ በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር የቀድሞ የሃገሪቱ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ባለፈው አመት በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።
የባራክ ኦባማ አስተዳደር የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ ከስልጣን መወገድን ተከትሎ ለግብፅ ሲሰጥ የነበረው ወታደራዊ ድጋፍ እንዲቀንስ አድርጎ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ የኦባማ አስተዳደር ለ አልሲሲ መንግስት ጀርባን ሰጥቶ እንደቆየም የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ።
የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ መንግስት ግብፅን ጨምሮ በሩሲያ እና በመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ዘንድ አዲስ የውጭ ፖሊሲን የመከተል ዕቅድ እንዳለው ይነገራል።