ኢሳት (የካቲት 14 ፥ 2009)
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በደቡብ ሱዳን ያለው ግጭት እልባት በሚያገኝበት ዙሪያ ላይ የሚመክር ልዑካን በተያዘው ሳምንት ወደ ጁባ እንደሚልኩ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ማክሰኞ ገለጹ።
የአሜሪካ የልዑካን ቡድን ከፕሬዚደንት ሳል-ባኪር ጋር ከሚያደርገው ውይይት ጎን ለጎን የተለያዩ የሃገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ምክክር እንደሚያካሄዱ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ዋቢ በማድረግ ሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ ዘግቧል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት የደቡብ ሱዳን መንግስትና በሪክ ማቻር የሚመራው አማጺ ቡድን ባለፈው አመት ስምምነት እንዲደርሱ ቢደረጉም ሁለቱ ወገኖች ዳግም ወደ ግጭት መግባታቸው ይታወሳል።
ይህንኑ አዲስ ግጭት ተከትሎ ሪክ ማቻር ከሃገሪቱ በመኮብለል በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ሲሆን፣ የሰላም አደራዳሪ ሃገር የነበረችው ኢትዮጵያ ማቻር ወደ ሃገሯ እንዳይገቡ እገዳን ጥላ ትገኛለች።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ አስተዳደር የደቡብ ሱዳን መንግስትና አማጺ ቡድኑ የሰላም ድርድር እንዲያደርጉ ግፊት ሲያሳድር መቆየቱ ይታወሳል።
አሜሪካ ሪክ-ማቻርን ያሳተፈ የሰላም ድርድር ቀጣይ እንዲሆን ብትፈልግም የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ማቻርን ገለል ለማድረግ እንዲወሰኑ የአማጺ ቡድኑ አመራሮች ቅሬታን ሲያቀርቡ መሰንበታቸው የሚታወስ ነው።
አዲሱ የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ይኸው በሁለቱ ወገኖች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በሰላም እንዲፈታ ለማድረግና በጉዳዩ ዙሪያ ከደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ጋር ለመምከር ውሳኔ መድረሱን ለመረዳት ተችሏል።
ከነገ በስቲያ ሃሙስ ይደርሳል ተብሎ የሚጠበቀው የአሜሪካ ልዑክ ከዚህ ቀደም የተደረሱ ስምምነቶች እንዴት ተግባራዊ መደረግ እንዳለባቸውና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚመክሩ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ገልጸዋል።
የአሜሪካ የልዑካን አባላት በደቡብ ሱዳን ጉዳይ ከዚህ በፊት በአደራዳሪነት ከተሳተፉ ሃገራት ጋር ተመሳሳይ ውይይት ያካሄዱ አያካሄዱ የተገለጸ ነገር የለም።
አዲሱ የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በአፍሪካ በሚደረጉ የሽብር እና የጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ከግብፅ ናይጀሪያ እና ደቡብ አፍሪካ መሪዎች ግር ምክክርን ያካሄደ ሲሆን፣ የልዑክ ቡድንን ወደ ጁባ ሲልክም፣ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በሪክ ማቻር ላይ የጣለውን እገዳ ተከትሎ የአማጺ አመራሩ ወደ ቀጠናው በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖን ያሳደረ ሲሆን፣ የሁለቱ ወገኖች ድርድር መቋረጥ በደቡብ ሱዳን አለመረጋጋት እንዲሰፍን ማድረጉን የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ።
በሃገሪቱ ጉብኝትን የሚያደርጉ የአሜሪካ የልዑካን አባላት ከአማጺያን ጋር ሊደረሰ በሚችሉ ስምምነቶች ዙሪያም ውይይትን ያካሄዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።