ዶ/ር ቴዎድሮስ ለአለም ጤና ድርጅት ሃላፊነት እንዳይመረጡ ቅስቀሳ ተጀመረ

ኢሳት (ሚያዚያ 11 ፥ 2008)

የኢትዮጵያውያ የሰብዓዊ መብት አቀንቃኝ ድርጅቶች ዶ/ር የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ለአለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተርነት እንዳይመረጡ ዘመቻ መጀመራቸውን አስታወቁ። በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው ኢትዮጵያን አድቦኬሲ ኔትወርክ  የሚባል ድርጅት ለአለም ጤና ድርጅት ዋና ሊቀመንበር ለሚስ ማሌና ፕሪሺየስ ማትሶሶ በጻፈው ደብዳቤ፣ ዶ/ር ቴዎድሮስ የአለም ጤና ድርጅት ለመምራት እውቀትና አቅም የሌላቸው ሰው መሆናቸውን ገልጿል።

የዶ/ር ቴዎድሮስ ለአለም ጤና ድርጅት ሃላፊነት እጩ መሆንም በአገለገሉበት በህወሃት መንግስት ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲ ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበትና ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዋና ተዋናይ እንደሆኑ ደብዳቤው ያስረዳል።

የዶ/ር ቴዎድሮስ ለአለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተርነት በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ብቸኛ ዕጩ ሆኖ መቅረብ ለአፍሪካ ህዝብ ንቀት እንደሆነ ኢትዮጵያን አድቦኬሲ ኔትወርክ በደብዳቤው አስፍሯል።

ዶ/ር ቴዎድሮስ የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሆነው ባገለገሉበት ወቅት የአስተዳደር ብልሹነት የታየባቸው፣ የማስተዳደር አቅም የሌላቸውና በአለም አቀፍ ደርጃ ኤድስና ቲቪ በሽታ ለመዋጋት የተሰጠውን ገንዘብ በአግባቡ በስራ ላይ ማዋል ያልቻሉ ሰው መሆናቸውን  ኢትዮጵያን አድቦኬሲ ኔትወርክ ለሚስ ማሌና ፕሪሺየስ ማትሶሶ በጻፉት ደብዳቤ አስረድቷል።

እኚህ ልምድ የሌላቸው ሰው በምን ምክንያት የአለም ጤና ድርጅት ሃላፊነት እጩ ሆነው ሊቀርቡ እንደቻሉ ግልጽ እንዳልሆነ ለሚስ ማትሶሶ አድቦኬሲው መልዕክቱን አስተላልፏል።