ኢሳት (የካቲት 16 ፥ 2009)
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፈዋል ተብለው በእስር ላይ የሚገኙት ዶ/ር መረራ ጉዲና ሃሙስ የተለያዩ የወንጀል ክሶች በይፋ ተመሰረተባቸው።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተግባራዊነትን የሚከታተለው ወታደራዊ ዕዝ ዶ/ር መረራ ጉዲና ከአውሮፓ ጉብኝታቸው በተመለሱ ጊዜ አዋጁን ጥሰዋል በሚል ለእስር ተዳርገው መቆየታቸው የሚታወስ ነው።
የዚህኑ ምርመራ መጠናቀቅ ተከትሎ አቃቤ ህግ ህገ-መንግስቱን በሃይል ለመናድ በሚሉና የተለያዩ ወንጀል ክሶች መመስረቱን አዲስ ስታንዳርድ የተሰኘ መጽሄት ዘግቧል።
በዚሁ ባለ 19 ገፅ የክስ ዝርዝር ዶ/ር መረራ በአንደኛ ሶስተኛና አራተኛ ክሶች ተካተዋል። የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ዳይሬክተር አቶ ጀዋር መሃመድ ተመሳሳይ ክስ በሌሉበት እንደተመሰረትባቸው ታውቋል።
ከሳሽ አቅቤ ህግ ሶስቱ ተከሳሾች ለአንድ አመት ያህል በኦሮሚያ ክልል ሲካሄድ በቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ በዋና አስተባባሪነት ተሳትፈዋል ሲል በክስ ሰነዱ አመልክቷል።
ሃሙስ በይፋ በተመሰረተው በዚሁ ክስ ኢሳት እና የኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ በሽብርተኛ የተከሰሱ ሲሆን፣ ሁለቱ የመገናኛ ተቋማት በሃገሪቱ ሲካሄድ የነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ እንዲባባስ አድርገዋል ተብለዋል። ሶስት የተለያዩ ክሶች በተናጠል የቀረበባቸው ዶ/ር መረራ ጉዲና በአውሮፓ ጉብኝታቸው ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር በመገናኘታቸውና በመወያየታቸው ክስ እንደተመሰረተባቸው ለመረዳት ተችሏል።
ዶ/ር መረራ ጉዲና ለአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ በሰጡት ቃለ-ምልልስ የተሳሳተና የመንግስትን ስም የሚያበላሽ መረጃ ሰጥተዋል በሚል በክሱ ተያይዟል። ተከሳሹ ለየትኛው የአሜሪካ ድምፅ ቋንቋ ክፍል ቃለ-ምልልሱን እንዳደረጉ የተገለጸ ነገር የለም።
ዶ/ር መረራ ጉዲና ሃሙስ ክስ በተመሰረተ ጊዜ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ቢጠበቅም የዳኞች ስልጠና እየተካሄደ ነበር በሚል ተከሳሹ ችሎት ሳይቀርቡ ቀርተዋል።
ክሱን የተቀበለው የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ከሁለት ሳምንት በኋላ ተለዋጭ ቀጠሮን ሰጥቷል። ዶ/ር መረራ ጉዲና በማዕከላዊ እስር ቤት እንዲቆዩ መደረጉንም ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
የህግ ባለሙያዎች በሶስቱ ተከሳሾች ላይ የቀረበው ክስ እስከ 10 አመት በሚደርስ ቅጣት የሚያስቀጣ መሆኑን እና የዋስትና መብት የሚከለክል እንደሆነ ለመጽሄቱ ገልጸዋል።