ዶ/ር መረራ በኢትዮጵያ መንግስት “ሽብርተኛ” ተብለው ከተፈረጁት አካላት ጋር አድርገውታል የተባለው መረጃ ምርመራ እየተካሄደበት መሆኑ ተገለጸ

ኢሳት (ታህሳስ 12 ፥ 2009)

በቅርቡ ለእስር የተዳረጉት ዶ/ር መረራ ጉዲና በኢትዮጵያ መንግስት በሽብርተኛ ቡድን ከተፈረጁት አካላት ጋር አድርገውታል የተባለው መረጃ ምርመራ እየተካሄደበት መሆኑን በቤልጅየም ብራሰልስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምላሹን ሰጠ።

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) አመራር የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና ከአውሮፓ ጉብኝታቸው በኋላ ለእስር የተዳረጉበት ሁኔታ ማብራሪያ እንዲሰጠው የአውሮፓ ፓርላማ ጥያቄን አቅርቦ እንደነበር ይታወሳል።

ለዚሁ ጥያቄ ምላሽን የሰጠው ኤምባሲው የፓርቲው አመራር ለእስር የተዳረጉት በሽብርተኛ ቡድን ከተፈረጁ አመራሮች ጋር አካሂደውታል የተባለን ውይይት መሰረት በማድረግ እንደሆነ መግለጹን አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል።

ኤምባሲው አክሎም ዶ/ር መረራ ጉዲና ከቡድኑ አመራሮች ጋር ተገናኝተው ከሆነ ድርጊቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚጥስ አካሄድ ነው ሲል በብራሰልስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አመልክቷል።

በአሁኑ ወቅት ለእስር ተዳርገው የሚገኙት ዶ/ር መረራ ጉዲና ከተባሉት አካላት ጋር ስለመገናኘታቸውና ውይይት ስለማካሄዳቸው ምርመራ እየተካሄደበት መሆኑን ኤምባሲው ምላሽን ሰጥቷል።

ይሁንና ዶ/ር መረራ ጉዲና ለእስር በተዳረጉት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚቆጣጠረው ኮማንድ ፖስት ከአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራሮች ጋር በመገናኘት በጋራ መግለጫን ሰጥተዋል ሲሉ ለህዝብ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ኮማንድ ፖስቱ ይህንን ቢልም በብራሰልስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዶ/ር መረራ ጉዲና በሽብርተኛ ቡድን ከተፈረጁ አካላት ጋር አካሄደውታል የተባለው መረጃ ምርመራ እየተካሄደበት እንደሆነ ይገልጻል።

ኤምባሲው አክሎም የኦፌኮ አመራሩ ለእስር የተዳረጉት ከአውሮፓ ፓርላማ ጋር በመገናኘታቸው ምክንያት እንዳልሆነ በመግለጫው ማመልከቱን አፍሪካ ኒውስ በዘገባው አስፍሯል።

በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ፍርድ ቤት ቀርበው የነበሩት ዶ/ር መረራ ጉዲና የ28 ቀን የምርመራ ጊዜ ተጠይቆባቸው በቀጠሮ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ፍርድ ቤት በቀረቡ ጊዜ በሰንሰለት ታስረው መታየታቸውን እማኞች በወቅቱ አስታውቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ከአስቸኳይ አዋጁ መውጣት በኋላ ለእስር ተዳርገዋል ከተባሉ ከ20ሺ በላይ ሰዎች መካከል 9ሺ 800 የሚሆኑት ረቡዕ መለቀቃቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ይሁንና ወደ አምስት ሺ የሚጠጉ ሰዎች ክስ የሚመሰረትባቸው እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ፈጽመውታል የተባለው ወንጀል ግን አልታወቀም።

አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በበኩላቸው ለእስር የተዳረጉ ሰዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጸምባቸዋል የሚል ስጋት መኖሩን በመግለጽ ላይ ናቸው።