ድርቁ ባጠቃቸው አካባቢ የሚኖሩ አርሶአደሮች ከፍተኛ ግብር ተጣለባቸው፡፡

ጥቅምት ፴ (ሠላሳ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአማራ ክልል ምስራቃዊ አካባቢዎች በዝናብ እጥረት ለረሃብ የተጋለጡ አርሶአደሮች በዚህ ችግር ላይ እያለን በአካባቢው አመራሮች ግብር እንድንከፍል በመገደዳችን ከፍተኛ ችግር ላይ ነን በማለት ተናገሩ፡፡
በድርቁ የተጎዱት አካባቢ የሚኖሩ የመንግስት ሠራተኞች በተለይ ለኢሳት ሲናገሩ ‹‹ የዝናቡ እጥረት እንዳለ ሆኖ መንግስት ለአርሶ አደሮች ግብአት አላቀረበም፡፡አርሶ አደሩ በዚህ ዓመት የሚቀምሰው አንዳች ነገር በእጃቸው ሳይኖር ግብር እንዲከፍሉ መገደዳቸው ከአንድ በህዝብ ተመረጥኩ ከሚል መንግስት የሚጠበቅ አይደለም ›› ይላሉ።
አካባቢው በድርቁ ምክንያት ምንም ዓይነት ሰብል እንዳላመረተ የሚናገሩት ተቆርቋሪ ሠራተኞች፣ አርሶ አደሩ አመቱን ለመዝለቅ ከገዥው መንግስትና ግብረሰናይ ድርጅቶች ዕርዳታ ሊቀርብላቸው ካልቻለ በእንስሳትና በሰው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡
በቅርቡ በጎንደር ከተማ በተካሄደ የባለሃብቶች ስበሳባ ላይ ‹‹በአማራ ክልል ግብር እየበዛ በመሆኑ ባለሃብቱ ወደ አጎራባች ክልል እንዲሄድ እተደረገ ነው፡፡›› በሚል ቅሬታ በአምራች ባለሃብቶች መቅረቡን የሚናገሩት አስተያየት ሰጪ፣ የክልሉ መንግስት ይህን ማሻሻል አለበት በማለት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
በተያያዘ ዜና በድርቁ ሙሉ በሙሉ በተጠቁ አካባቢዎች የደረሰውን ጉዳት የሚገልጹት አርሶ አደሮች በማሽላ እና ማሾ ምርቶች ላይ ክፍተኛ ጉዳት እንደ ደረሰ ተናግረው ለቀጣይ ዓመት የሚሆን በቂ ምርት አላገኘንም ይላሉ፡፡
የሚሰጠው እርዳታም ሁሉን ያላካተተ በመሆኑ ከፊሉ አርሶ አደር እየተጎዳ መሆኑን የሚናገሩት ተጎጂዎች በድርቁ ሙሉ በሙሉ በተጠቁ አካባቢዎች የተሰጠው ዕርዳታም በቂ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡እርዳታውን ያላገኙ በርካታ ተጎጂዎች ቢኖሩም ‹‹ በጣም የተጎዳ ብቻ እናስተናግዳለን ›› በማለት ይሻላሉ የተባሉትን ተጎጂዎች በእርዳታው ያልማቀፍ አሰራር መታየቱን ተጎጂው ተናግረዋል፡፡ በአካባቢው እንስሶችም በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዱ ሲሆን ነዋሪውም በችግሩ ከሰውነት እየወጣ መሆኑን ተጎጂ አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ምስራቃዊ አካበቢዎች በድርቁ ከታሰበው በላይ የተጎዳ የህብረተሰብ ክፍል እንዳለ ሰሞኑን አካባቢውን በከፊል ተዘዋውረው ለጎበኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ነዋሪዎች መናገራቸውን የደረሰን መረጃ ያመላክታል፡፡
ከዚሁ ከድርቅ ዜና ሳንወጣ በኢትዮጵያ በርሃብ ምክንያት በቀን ከሁለት ሕጻናት በላይ እንደሚሞቱ ቢቢሲ ዘግቧል።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያለው ድርቅ አድማሱን ያሰፋና አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አፋጣኝ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው 15 ሚሊዮን የሚሆኑ የድርቅ ተጠቂዎች መኖራቸውንና አፋጣኝ ዕርዳታ ካልተሰጣቸው ወደ ከፋ ሁኔታ እንደሚቀየር እንዲሁም የ1977 ዓ.ም ዓይነት ዘግናኝ ረሃብ ማንዣበቡን በዚህም ሳቢያ በየቀኑ ከሁለት በላይ ታዳጊ ሕጻናት በሞት እንደሚቀጠፉ ቢቢሲ ከስፍራው ዘግቧል።
በተለይ በትግራይ፣አማራ፣ሶማሊያና አፋር ክልሎች ሕጻናት በምግብ ዕጥረት በሚመጣ በሽታ መጠቃታቸው እንዲሁም የዝናቡ ዕጥረት በፈጠረው ድርቅ አርብቶ አደሮች ከብቶቻቸው እያለቁባቸው መጻኢው ዕድላቸው ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ መግባቱን ጉዳተኞቹ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ አፋጣኝ የእርዳታ እጁን እንዲዘረጋ ተማጽኖውን አቅርቧል።
የኢትዮጵያ መንግስት ርሃቡን ለመግታት እና ለጉዳተኞች ለመድረስ መርሃ ግብር ነድፎ አፋጣኝ እርዳታ ከማቅረብ ይልቅ የፖለቲካ ፍጆታ ለማግኘት ገጽታ ግንባታ ላይ ማተኮሩና የርሃቡን ስቃይ ካለመረዳት የፖለቲካ ፓርቲዎች ዓመታዊ በዓላቸውን በደማቅ ሁኔታ ለማክበር እየተረባረቡ ይገኛሉ ብአዴን በቅርቡ ሕዳር ወር ለሚያከብረው በዓሉ 300 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡ ይታወሳል።
ዩኒሴፍ ዛሬ በላከው መረጃ ደግሞ በኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 2 ወራት ውስጥ 350 ሺ ህጻናት ከምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ በሽታ በመጠቃታቸው ህክምና ያስፈልጋቸዋል ብሎአል።