ሚያዝያ ፲፫(አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ድምጻችን ይሰማ፦”ኢ–ሰብአዊነትንና ሽብርን ደግመን እናውግዝ! ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን እንታደግ!”በሚል ርእስ ባወጣው መግለጫ በደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያውያን እና ሌሎችም አፍሪካውያን
ዜጎች ላይ አሰቃቂ የግድያ ወንጀል እየተፈጸመባቸው እንደሚገኝ በመጥቀስ፤ ሰቅጣጩ የጭካኔ ምግባር አፍሪካዊያን ላይ በአፍሪካዊያን የሚፈፀም መሆኑ ደግሞ ይበልጥ አሳዛኝ ያደርገዋል ብሏል።
ከአስርት ዓመታት በፊት ምእራባዊያን ደቡብ አፍሪካዊያን የሚያደርጉትን የፀረ-አፓርታይድ ትግልና መሪያቸውን ኔልሰን ማንዴላን በ«ሽብርተኝነት» ፈርጀው ሳለ ኢትዮጵያና ሌሎች አፍሪካዊያን ሀገሮች ትግላቸውን እንደደገፉ ያስታወሰው ድምጻችን ይሰማ፤
ይህ ታላቅ ውለታ ተዘንግቶ የተፈፀመው እና ሰሞኑን እያየነው ያለውን የጥላቻና የግፍ ግድያ ሰብአዊ ፍጡር ሁሉ ሊያወግዘው ይገባል።”ብሏል።
“ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችም ይህንን ተግባር በአንድ ድምፅ እናወግዛለን እንቃወማለንም፡፡” የሚለው ድምጻችን ይሰማ፣ “በሊቢያም በክርስትያን ወገኖቻችን ላይ አይሲስ በተባለው የሽብር ቡድን የተፈፀመው አሰቃቂ ተግባርም አውግዟል።
ይህ ስብስብ የሚሰራውን አሰቃቂ የግፍና የሽብር ተግባር «እስላማዊ» ካባ ሊያላብስ ቢሞክርም፤ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሙስሊሞች በአንድ ድምፅ አውግዘውታል፡፡” ብሏል።
” ጌታችን አላህ በቅዱስ ቁርአን አንድን ነፍስ ያለአግባብ መግደል ሁሉንም ሰብአዊ ፍጡር መግደል እንደሆነ፣ በአንፃሩም አንድን ነፍስ ህያው ማድረግ ሁሉንም ሰው ህያው እንደማድረግ መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ ገልፆዋል።” የሚለው ድምጻችን ይሰማ፤
” ይህ አባባል የሰብአዊ ፍጡርን ሕይወት ዋጋ ትልቅነት የሚያሳይ መሆኑን በርካታ የእስልምና ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡”ሲል ገልጿል።
“አይሲስ የተባለው የሽብር ቡድንና «የእሱን ፈለግ እንከተላለን» የሚሉ ሌሎች ቡድኖች ሙስሊሙንም፣ ክርስትያኑንም በግፍ ሲገድሉ ቆይተዋል፡፡ ከህጻናት እስከ ዩኒቨርሲቲ ያሉ ተማሪዎችን በማደሪያ ቦታቸውና በትምህርት ቦታቸው ባሉበት ገድለዋል።
ለአምልኮ የተሰባሰቡ ሰዎችን በመስጊድም፣ በቤተ ክርስቲያንም ጨፍጭፈዋል፤ በስደትም ይሁን «በበጎ አድራጎት ተግባር ላይ እንሰማራለን» ብለው ወደሌላ አገር የተጓዙ የሌላ አገር ዜጎችንም ሳይቀር እንደዋዛ በአሰቃቂ ሁኔታ ገድለዋል፡፡
” ሲልም በመግለጫው አትቷል።
“ይኸው ትናንት በተሰማ ዜና ደግሞ 28 ኢትዮጵያውያን የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ወንድሞቻችን በሊቢያ በአሰቃቂ ሁኔታ በሽብር ቡድኑ ተገድለዋል።”ያለው ድምጻችን ይሰማ፤ “እንደዚህ አይነቱን የሽብር ተግባር በእርግጥም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሙስሊም
ከማውገዝ ባሻገር- እንደሙስሊምነቱና እንደዜግነቱ አላህ በሰጠው ችሎታ ለመከላከል የበኩሉን ስራ መስራት አለበት፡፡”ብሏል።
በተለያዩ ሀገራት በስደት ላይ ሆነው ህይወታቸው ከፍተኛ ችግር ላይ ለወደቁ ዜጎች በተገኘው ቀዳዳ ድጋፍ የመስጠት ስራ ላይ መሳተፍ አስፈላጊ እንደሆነም ድምጻችን ይሰማ ጠቁሟል።
ከፖለቲካ ድርጅቶች ደግሞ መድረክ እና 9 ፓርቲዎች ትብብር በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ ተግባር አውግዘው፣ ስደት የገዢው ፓርቲ ፖሊሲ መበላሸት ውጤት ነው ብለዋል።