ሐምሌ ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አቶ አቡበክር አህመድን ጨምሮ በ18 የድምጻችን ይሰማ የመፍትሄ አፈላላጊ የኮሚቴ አባላት ላይ የተላለፈውን የፍርድ ውሳኔ “ድራማ ነው” በማለት ያጣጣለው ድምጻችን ይሰማ ፣የተሰጠው ፖለቲካዊ ፍርድ “ትግሉን የበለጠ እንድንቀጥልበት ያደርገናል” ሲል ገልጿል።
የፍርዱን ኢ-ፍትሃዊነት የመንግስት ባለስልጣናትና ድራማውን የተወኑት አቃቢ ህግጋት እና ዳኞች ሳይቀር ያውቁታል የሚለው ድምጻችን ይሰማ፣ ውሳኔው ” የበለጠ እንታገል ዘንድ የሚያነሳሳ ምክንያት እንጂ ከትግል የሚያርቅ ሰበብ ” አይደለም ብሎአል።
ውሳኔውን የጠበቀው በመሆኑን የገለጸው ድምጻችን ይሰማ፣ ትግሉ ረጅም መሆኑንም በመግለጫው ሳይጠቅስ አላላፈም። ትግሉን በአካባቢ በተደራጀ መልኩ ለመቀጠል እንዲሁም ሰላማዊ የሚባሉ የትግል አማራጮችን ተግባራዊ ለማድረግ ማቀዱንም ገለጿል።በተመሳሳይ ዜና ደግሞ አርበኞች ግንቦት7 ውሳኔውን “ፍርደ-ገምድል” ሲል በጽኑ አውግዞታል።
ንቅናቄው በመግለጫው ፣ “በደል ደርሶብኛልና ልሰማ” ብሎ አቤቱታ ያቀረበ ሕዝብ መሪዎችን እስከ ሃያ ሁለት ዓመታት በእስር መቅጣት የአገዛዙ እብሪትና ማናለብኝነት አጉልቶ የሚያሳይ ተግባር ነው። “ብሎታል።
“ፍርደገምድል ውሳኔ የተሰጠው ፕሬዚዳንት ኦባማ በአገራችን መዲና ተገኝተው “ለሰላም ሲባል ነፃነትን ማፈን ሁለቱንም ያሳጣል” ባሉ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መሆኑ፣ አገዛዙ የሚሰማ ጆሮ የሌለው መሆኑን የሚያረጋግጥ ሆኗል” የሚለው አርበኞ- ግንቦት7 ፣ የሙስሊም መሪዎች በእስር ላይ በነበሩት ጊዜ በምርመራ ስም መደብደባቸውን፤ ክብራቸው መደፈሩን፤ የተለያዩ ዘግናኝ ሰቆቃዎች ተፈጽሞባቸው እንዲሁም የሀሰት ዶክመንታሪ ፊልሞች እንዲሰራጩ ተደርገው ስማቸውን ለማጥፋት ሙከራ መደረጉንም አስታውሷል።
“በሙስሊም ወገኖቻችን ላይ የደረሰው በደል ሃይማኖት ሳይለይ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ላይ የደረሰ በደል በመሆኑ፣ መፍትሄ በጋራ ህወሓትን በማስወገድና በምትኩ ፍትህ፣ ነፃነት፣ ዲሞክራሲና የአገር አንድነት የሚጠብቅ የመንግሥት ሥርዓት ማቆም ሲቻል ብቻ ነው ብሎአል።