ድህነት መቀነሱን የሚያሳይ በገልለልተኛ ወገን እስካልተሰራ ድረስ ተቀባይነት የለውም ተባለ

መጋቢት ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ከሳምንት በፊት የአቶ መለስ ዜናዊ ባለቤት በተገኙበት አንድ ጉባኤ ላይ የገንዘብ ሚኒስቴር ያስጠናው የድህነት ቅነሳ ሪፖርት ይፋ መሆኑ ይታወሳል። ጥናቱ ድህነት በኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ መሄዱን የሚያመለክት ሲሆን፣ የመንግስት የመገናኛ ብዙሀንም ዜናውን ተፈላጊው ህዝብ ዘነድ ለማዳረስ ሲደክሙ ሰንብተዋል።

ይሁን እንጅ ገለልተኛ ባለሙያዎች የጥናቱን ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ሀሳቦችን በመሰንዘር ላይ ናቸው። አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ኢኮኖሚስት እንዳሉት፣ ጥናቱን ያካሄደው የገንዘብ ሚኒስቴር መሆኑ በራሱ የጥናቱን ተአማኒነት ገደል የሚከተው ነው። ያም እንኳ ቢሆን ጥናቱ ሆን ተብሎ የመንግስትን ፖሊሲ ለመደገፍ ተደርጎ የተሰራ በመሆኑ ተቀባይነት አይኖረውም።

ምሁሩ እንዳሉት ጥናቱ የድህነነት ወለል መመዘኛ ማስፈርት ብሎ ያስቀመጠው ጣሪያ ከሌሎች አገሮች ጋር  ሲነጻጸር ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እንኳ አብሮ የማይሄድ ነው። በጥናቱ ውስጥ የምግብ የድህነት ወለል እና አጠቃላይ የድህነት ወለል ተብለው የቀረቡት አሀዞች 1985 እና 3781 ብሮች በተከታታይ መሆናቸውን ያወሱት ምሁሩ፣ በጥናቱ መሰረት አንድ ሰው ከድህነት ወለል ወጣ የሚባለው በአመት ውስጥ 1985 ብር ወይም 110 ዶላር ለምግብ ፍጆታ ሲያውል መሆኑን ጠቁመዋል። ይህም አሀዝ በቀን ውስጥ ሲሰላ አንድ ሰው ከድህነት ወጣ የሚባለው በቀን ዜሮ ሰላሳ ሳንቲም ያገኘ እንደሆነ የሚያመለክት ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ገንዘብ ሲሰላ ዜሮ ሰላሳ ዶላር ማለት 5 ብር ሲሆን፣ አሁን ባለው የገበያ ሁኔታ 5 ብር ሁለት ደረቅ እንጀራ ብቻ እንደሚያስገዛ ጠቁመዋል። በተለምዶ ቀይ ወጥ እየተባለ የሚጠራው ምግብ በትንሹ 15 ብር እንደሚሸጥ ያወሱት ምሁሩ ከ30 በመቶ በላይ ወይም ወደ 25 ሚሊዮን የሚጠጋው ኢትዮጵያ አንድ ቀይ ወጥ በልቶ ለመዋል ሶስት ቀን ምንም ምግብ ሳይመገብ ገንዘቡን ማጠራቀም አለበት ሲሉ አስረድተዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ምሁሩ አለም የሚከተለው በቀን አንድ ዶላር የሚለው ድህነነት ወለል መለኪያ ጋር ለመድረስ ብዙ አመታትን መጠበቅ ግድ ይላል ይላሉ።

የመለስ መንግስት ድህነት ቀንሷል ብሎ በይፋ የሚናገረው በዚህ የቁጥር ጨዋታ ነው የሚሉት ምሁሩ፣ በዚህ ጥናት የተሳተፉት ምሁራን ያስተማራቸውን ህዝብ ለማታለል ሙያቸውን በመሸጣቸውም ወቅሰዋቸዋል።

ምንም እንኳ የድህነት መለኪያ መስፈርት እንደየአገሩ ተጨባጭ ሁኔታ ቢወሰንም በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን በሚታየው የኑሮ ሁኔታ አንድ ሰው በወር 321 ብር ወይም 17 ዶላር እያገኘ ምግቡን ፣ የቤት ኪራዩን እና ሌሎች ወጪዎቹን ሸፍኖ በህይወት ሊኖር አይችልም ብለዋል። የመለስ መንግስት 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎችን ባለፉት 7 አመታት ከድህነት መንጥቀን አወጣን እያሉ የሚናገሩት 2 ሚሊዮን ሰዎችን በቀን 2 ደረቅ እንጀራ እንዲገዙ ወይም ቁርስና ምሳቸውን ሳይመገቡ በሶስት ቀን አንድ ጊዜ አንድ ቀይወጥ እንዲመገቡ በመስቻላቸው ነው ሲሉ ጥናቱን ኮንነዋል።

ሰሞኑን የመንግስት የገንዘብ ሚኒስቴር ባለስልጣናት ለወ/ሮ አዜብ ድህነት መቀነሱን ለማስረዳት ሲጣጣሩ መታየታቸውን ፎርቹን ጋዜጣ በስእህል አስደግፎ ዘገባ ማቅረቡ ይታወሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide