(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 6/2010)
የወልቃይት አማራ ማንነት ኮሚቴ አባላት የግራ ዳኛው ዘርአይ ወልደሰንበት ከችሎት እንዲነሱላቸው ያቀረቡትን ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አደረገው።
ተከሳሾቹ ዳኛው እኛ አማራ ስለሆንን ፍትሃዊ ዳኝነት እንገኛለን ብለን አናምን የሚል ቅሬታ አንስተዋል።
ፍርድ ቤቱ በበኩሉ ዳኛው አማራ በዘሩ የማይኮራ፣በጎጥ የሚጠራ ህዝብ ነው ያሉት ሀሳብ ከተከሳሾቹ ጉዳዩ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም ሲል ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል።
የወልቃይት ሕዝብ የአማራ ማንነት አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት አቶ መብራቱ ጌታሁን ፣ አቶ ጌታቸው አደመ ፣ አቶ አታላይ ዛፌ ፣ አቶ አለነ ሻማና አቶ ነጋ ባንተይሁን በግራ ዳኛው ዘርአይ ወልደሰንበት ላይ አቤቱታቸውን ሲያሰሙ ዳኛው በወልቃይት የአማራ ማንነት ላይ ግልጽ የሆነ የፖለቲካ አቋማቸውን የሚያራምዱ መሆናቸውን በተለያዩ መድረኮች ያንጸባርቃሉ።
ወልቃይትን በተመለከተ አማራ በማንነቱ የማይኮራ፣ በጎጥ የሚጠራ ህዝብ ነው የሚል ከትግራይ ህዝብ ጋር በማነፃፀር ሰፊ የዘረኝነት አስተሳሰብ ሲያራምዱ ታይተዋል ይላል የተከሳሾቹ አቤቱታ።
የአማራ ተወላጅ የሆኑት እነዚህ ተከሳሾች ዳኛው ይህን አስተሳሰብ ይዘው ፍትሃዊ ዳኝነት ሊሰጡን አይችሉም በሚል ከችሎት እንዲነሱ ተቃውሟቸውን አቅርበው ነበር።
ተከሳሾቹ አዋጅ 25/1988 አንቀፅ 27 (1) ከሀ እስከ ሠ ያሉትን ድንጋጌዎችም በማመልከቻቸው ላይ ጠቅሰዋል።
በዚህ አንቀጽ መሰረትም አንድ ዳኛ ተቃውሞ ከቀረበበት በግድ እዳኛለሁ ማለት ስለማይችል ራሱን ከችሎት ያነሳል።
ነገር ግን ማመልከቻው ከቃል አልፎ በጽሁፍ የቀረበለት የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት በዳኛው ላይ የቀረበበውን አቤቱታ ወደ ጎን በማለት ዳኛው ሀሳባቸውን እንዲሰጡ መፍቀዱን ነው መረጃዎቹ ያመለከቱት።
የግራ ዳኛው ዘርአይም ህገ መንግስቱ የሰጠኝን ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ተጠቅሜ የአማራ ህዝብን በተመለከተ አስተሳሰቤን አራምጄያለሁ ሲሉ ከአንድ የህግ ባለሙያ የማይጠበቅ ማላሽ ሰጥተዋል ይላሉ በችሎቱ የነበሩ ታዛቢዎች።
በችሎቱ የቀሩት ሁለት ዳኞችም በሆርን አፌርስ ላይ ዳኛው ዘርአይ አሰፈሩት የተባለውን ጽሁፍም ሆነ ለአቤቱታው የሰጡትን ምላሽ በሌሎች ዳኞች ማስመርመራቸውን ተናግረዋል።
በዚሁ መሰረትም ዳኛው ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብታቸውን ተጠቅመው የሰጡት አስተያየት መሆኑን ተረድቼያለሁ ሲሉ በችሎቱ የቀሩት ሁለቱ ዳኞች ምላሽ ሰጥተዋል።
በዚሁ መሰረትም ዳኛ ዘርአይ ያራመዱት አስተሳሰብ ከተከሳሾቹ ጉዳይ ጋርም የሚያገናኘው ነገር የለም በሚል የተከሳሾቹን አቤቱታ ውድቅ አድርጎታል።
ኢሳት ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ዘገባውን ባቀረበበት ወቅት የህግ ባለሙያው ዶክተር ስማህኝ ጋሹ ከህግ አግባብ የተከሳሾቹ ጥያቄ ትክክል ነው ብለው ነበር።