ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ በሃይል እጥረት ሳቢያ ለማምረት አለመቻሉን ለደንበኞቹ ገልጸ፡፡

ነሃሴ  ፲፫ ( አሥራ  ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በመላው አማራ የህውሃት/ኢህአዴግን ምርት ላለመጠቀም በተማማለው ህዝብና ነጋዴ ምክንያት ተጠቃሚ ያጣው  የሞሰቦ ስሚንቶ ምርት ወደ ገበያ ለማስገባት አገዛዙ  የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካን በኃይል በመቆራረጥ ምርቱን ለደንበኞቹ ለማቅረብ እንዳይችል ማድረጉን ምንጮች ገለጹ:፡

የክልሉ ነጋዴዎች በአማራው ህዝብ ላይ የሚደረሰውን ግፍና ግድያ ለመቃወም የመሰቦ ስሜንቶ ምርትን ላለመጠቀም የወሰኑ ሲሆን፣ ድርጊቱ ያበሳጨው ህወሃት መራሹ መንግስት በአማራጭነት የሚቀርበው እና በናይጀሪያዊው ባለሀብት የተቋቋመው ፋብሪካ ምርቱን ወደ ክልሉ እንዳያደርስ ጫና ፈጥሮበታል። ከአንድ ወር በፊት ከዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ያዘዙ ነጋዴዎች ሲሚንቶ እንዳይደርሳቸው ሆን ተብሎ በፋብሪካው ላይ የሃይል መቆራረጥ እንዲከሰት በማድረግ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ነጋዴዎችና የፋብሪካው ምንጮች ለዘጋቢያችን ተናግረዋል፡፡

ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ምርት በመላ ሃገሪቱ ተፈላጊ እየሆነ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ከአሁን በፊት ሲያመርትበት በነበረው ፍጥነት እንዳያመርት ጫና እየተደረገበት በመሆኑ በትዕግስት እንዲጠባበቁ ለደንበኞቹ ማስታወቅ ጀምሯል።

በመላ ሃገሪቱ የሚያደርሰውን ግድያ በመቃወም  ኢትዮጵያውያን የህወሃት ኩብንያ ምርቶችን መጠቀም እያቆሙ ነው፡፡በተለይ በአማራ ክልል ህዝቡ ዳሸን ቢራን ጨምሮ  ማንኛውንም የህወሃት ኢህአዴግን ኩባንያ ምርቶች መጠቀም አቁሟል።