(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 10/2010) በፋሲል ከነማ የክለብ አርማ ስም ዳሽን ቢራ ፋብሪካ ጃኖ የሚል ቢራ ለማስተዋወቅ ነገ በጎንደር ባዘጋጀው ኮንሰርት ላይ ህብረተሰቡ እንዳይካፈል የአካባቢው ወጣቶች አስጠነቀቁ።
ባላገሩ በሚል ይዞ የመጣው ቢራ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ለኪሳራ የተዳረገው ዳሽን ቢራ ፋብሪካ አሁን ደግሞ ጃኖ በሚል አዲስ ቢራ ለማስተዋወቅ መዘጋጀቱ ከንቱ ሙከራ ነው ሲሉ ወጣቶቹ ተቃውሞአቸውን ገልጸዋል።
ኮንሰርቱ የኦሮሞ ወገኖቻችን እየተገደሉ ባሉበት መዘጋጀቱና ከጃኖ ቢራ ሽያጭ በሚገኝ ገቢ የጦር መሳሪያ እንዲገዛም አንፈቅድም ብለዋል የጎንደር ወጣቶች።
ከዳሽን ቢራ የሚገኝ ብር ለገዳዮቻችን የጥይት መግዣ እንዲሆን አንፈቅድም በሚል የጎንደር ወጣቶች ጃኖ በሚል ቢራ ስም የተዘጋጀውን ኮንሰርት ተቃውመዋል።
ይህ አዲሱ ጃኖ ቢራ ባላገሩ በሚል ሊሸጥ ታስቦ የነበረው ምርት በባህርዳር ወጣቶች ከከሸፈ በኋላ ሕዝብን ለማታለል የተፈጠረ መሆኑን ወጣቶቹ ይናገራሉ።
ጃኖ ቢራን ሆን ብሎ በሕዝብ ዘንድ ከሚወደደው ፋሲል ከነማ ጋር ለማስተሳሰር መሞከሩም አገዛዙ ምን ያህል መሰሪና አጭበርባሪ መሆኑን ያሳያል ሲሉ ወጣቶቹ ተናግረዋል።
በዚሁ ቢራ ስም ነገ መስከረም 11/2010 የተዘጋጀውን የሙዚቃ ኮንሰርትም ተቃውመዋል።
በአሁኑ ጊዜ የኦሮሞ ወገኖቻችን በሕወሃት አጋዚ ሃይሎች እየተገደሉ ባሉበት ጊዜም የሙዚቃ ኮንሰርት በጎንደር መዘጋጀቱንም አጥብቀን እንቃወማለን ነው ያሉት።
እናም የጎንደርና የአካባቢው ሕዝብ በኮንሰርቱ እንዳይሳተፍ ወጣቶቹ ጥሪ አቅርበዋል።
በኮንሰርቱ ለመሳተፍ በሕወሃት አባላት የሚታገዙ የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ነን የሚሉ ሁሉ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም ወጣቶቹ አስጠንቅቀዋል።
በኮንሰርቱ 3 ወጣት ድምጻውያን ዝግጅታቸውን እንደሚያቀርቡ ለዚሁ ተብሎ የተዘጋጀው የማስታወቂያ ፖስተር ይገልጻል።
እነሱም ያሬድ ደጉ፣ሳሚ ደንና ብስራት ሱራፌል የተባሉ ሙዚቀኞች ናቸው።
ወጣቶቹ በሕዝብ ደም ላይ ለመዝፈን ያቀዱትን ሙዚቀኞች በመቃወም ሕብረተሰቡ በኮንሰርቱ እንዳይሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።