ዳሸን ቢራ “ባላገሩ ቢራ” በሚል የስያሜ ለውጥ በባህርዳር ከተማ ባዘጋጀው ኮንሰርት ላይ በፈነዳው ቦምብ 2 ሰዎች መሞታቸውና 31 ሰዎች መቁሰላቸው ተነገረ።

ሚያዝያ ፳፫ ( ሃያ ሦስት ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ዛሬ በባህር ዳር የጅምላ አፈሳ ሲካሄድ ውሏል።
ኮንሰርቱ እየተካሄደ ያለበት ሥፍራ በሁለት ተከታታይ የቦምብ ፍንዳታዎች መናወጡን ተከትሎ ፕሮግራሙ ሙሉ በሙሉ የተቋረጠ ሲሆን፣ በርካታ ታዳሚዎች በፖሊስ ተከበው ወደ እስር ቤት ተወስደዋል።
ኮንሰርቱ ላይ ሙዚቃ ስትጫዎት ፍንዳታ በመሰማቱ ክፉኛ የደነገጠችውን ድምጻሚ ኩኩ ሰብስቤን ጨምሮ ከባድና ቀላል የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች ወደ ፈለገ ህይወት ሆስፒታል ተወስደው ህክምና የተደረገላቸው ሲሆን፤እስካሁን ለተፈጸመው ፍንዳታ ኃላፊነቱን የወሰደ አካል የለም።
ከፍንዳታው በኋላ የተኩስ ልውውጥ መደረጉን የሚገልጹት ምንጮች፤ ከ31ዱ ቁስለኞች መካከል በተኩስ ልውውጡ የተመቱ እንዳሉበት አመልክተዋል።
በሌላ በኩል ዳሸን ቢራ “ ባላገሩ ቢራ” በማለት ስላዘጋጀው ኮንሰርት ድርጅታቸው ምንም የሚያውቀው ነገር እንደሌለ የባላገሩ ኢንተርቴይንመንት ኃላፊ አርቲስት አብርሐም ወልዴ ገልጿል።
ዳሸን ቢራ ባላገሩ አይዶልን ስፖንሰር ሲያደርግ እንደነበር ይታወቃል። ይህ ቢሆንም ሌላው ቀርቶ “ባላገሩ”የሚለውን የድርጅታቸውን ስያሜ ለቢራ ስያሜ ሲወስዱት እንዳላማከሯቸው አርቲስት አብርሐም ተናግሯል።
ከዚህም ባሻገር በኮንሰርቱ ከተጋበዙት አርቲስቶች መካከል አንጋፋዎቹ እነ ማህሙድ አህመድ በዝግጅቱ ላይ አለመገኘታቸው ታውቋል።
የብአዴን የንግድ ድርጅት የሆነው የጥረት ኮርፖሬሽን አንድ አካል እንደሆነ የሚነገርለት ዳሸን ቢራ ከተቋቋመ ሁለት አስርት ዓመታትን ቢያስቆጥርም የአምባገነኖች አገልጋይ ከመሆን አልፎ ለተቋቋመበት አካባቢ ሕዝብ ምንም የፈየደው ነገር እንደሌለ የቅርብ መረጃ ያላቸው አካላት ይናገራሉ።
ሌላው ቀርቶ ከተሞች የየራሳቸውን የአገልግሎት ገቢ እንዲሰበስቡ በተሰጣቸው ስልጣን መሰረት የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከዳሸን ማግኘት ያለበትን የዓመታት የአገልግሎት ገቢ ማግኘት እንዳልቻለ የአስተዳደሩ ምንጮች ይገልጻሉ።
ከአማራ ሕዝብ ጥቅም ይልቅ ለህወኃት አለቆቻቸው ጥብቅና በቆሙት በብአዴን አመራሮቹ በእነ ታደሰ ጥንቅሹ የሚዘወረው ድሸን ቢራ ለጎንደር ከተማ የአገልግሎት ዕዳውን 38 ሚሊዮን ብር እንዲከፍ በተደጋጋሚ ቢጠየቅም አሻፈረኝ ማለቱን የሚጠቅሱት ምንጮች፤ ለተቋቋመበት ከተማ ያለበትን ዕዳ ከመክፈል ይልቅ ለመቀሌ ስታዲዬም ማሰሪያ 42 ሚሊዮን ብር መስጠቱን ያወሳሉ።
“ለመቀሌ ስታዲየም ለምን 40 ሚሊዮን ብር ለገሰ አይደለም ቅሬታችን? መቶ ሚሊዮን ብርም ቢለግስ ደስታችን ነው። የኛ ጥያቄ ዕዳን ከመክፈልና ከልገሳ የትኛው ይቀድማል የሚል ነው።” ሲሉ የአስተዳደሩ ሠራተኞች ይገልጻሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ የጅምላ አፈሳ ሲደረግ ውሏል።
ወታደሮች በኦራል መኪናዎች በመሆን ሰፈር ለሰፈር በመግባት ወጣቶችን ከማፈሳቸውም ባሻገር በየመጠጥ ቤቶች ጭምር በመግባት ያገኙትን ሰው ሁሉ ሲጭኑ ውለዋል።
በከተማዋ በስፋት የተሰማሩት ወታደሮች ምን ያህል ሰዎችን እንደያዙ ማረጋገጥ ባይቻልም ፤ አፈሳው የጅምላ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።