ሰኔ ፳፯ ( ሃያ ሰባት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ታዋቂው የቢዝነስ ጋዜጣ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዙሪያ ይዞት በወጣው ጽሁፍ እንዳተተው ምንም እንኳ ቻይና መራሹ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የስራ እድል በመፍጠር በአገሪቱ ውስጥ የሚታየውን የስራ አጥ ቁጥር ትክክለኛ አካሄድ መስሎ ቢታይም፣ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የሆኑ ዲፕሎማቶች አጠቃላይ የኢኮኖሚ እቅዱ ይሳካል የሚል እምነት የላቸውም።
ዲፕሎማቶቹ ከሚጠቅሷቸው ምክንያቶች መካከል የፋይናንስ አገልግሎቱ ፣ የሸቀጦችና የቴሌኮም አገልግሎቱ ለውጭ አገር ዜጎች የተከለከሉ መሆናቸውና ገዢው ፓርቲ የግል ባለሃብቶችን በጥርጣሬ ማየቱ የሚሉት ይገኙባቸዋል።
ምንም እንኳ አሁን ያለው ፖሊሲ የስራ እድል በመፍጠርም ሆነ ሌሎችን የኢኮኖሚ እቅዶች ለመተግበር የሚያግዝ የውጭ ኢንቨስትመንት መሳብ የቻለ ቢሆንም፣ መንግስት ከፖለቲካና ከሲቪክ መብቶች ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ባለመቻሉ የመጨረሻው ውጤት እንደማያምር የሚገልጹ ሰዎች ቁጥር እየተባረከቱ መምጣታቸውን ጋዜጣው ጠቅሷል።
በቅርቡ በሃዋሳ የተገነባው የኢንዱስትሪ ሰፈር ተስፋ የሚሰጥ ቢሆንም፣ ከሃዋሳ በስተሰሜን የአንድ ሰአት ጉዞ በሁዋላ ያለው እውነታ ፣ የኢኮኖሚ ታዕምር ፈጥሮአል እየተባለ የሚነገርለት ፖሊሲ በድቡሽት አፈር ላይ የቆመ መሆኑን ያሳያል ብሎአል። በዝዋይ አቅራቢያ በመንገዶች ላይ የሚታዩት የተቃጠሉ አውቶቡሶች እና የጪነት መኪኖች ላለፉት 25 ዓመታት ስልጣኑን ተቆጣጥሮ የሚገኘውን የትግራይ ነጻ አውጭ ድርጅት ለመቃወም ለ11 ወራት ሲደረግ የነበረውን ህዝባዊ ትግል የሚዘክሩ ሃውልቶች ናቸው ሲል ጋዜጣው አትቷል።
በዚህ ተቃውሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ ምናልባትም ከ1 ሺ በላይ መገደላቸውን፣በአስር ሺዎች የሚቆጠሩትም መታሰራቸውንና ብዙዎቹ ከ5 ሳምንታት የፖለቲካ ስልጠና በሁዋላ መለቃቀቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።
ጭካኔ የተሞላበት የሃይል እርምጃ መጠነኛ ሰላም አስፍኗል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም እስከ ነሃሴ ወር ተራዝሟል፤ ነገር ግን አሁንም የትጥቅ ትግል የሚያካሂዱ ኢትዮጵያውያን በደንብ እየተንቀሳቀሱ ነው፣ ይህንንም መንግስት ያምናል በማለት በአገሪቱ ውስጥ ስለሚካሄደው ትግል እውቅና በመስጠት ዘግቧል።
ጋዜጣው በመደምደሚያው ፣ ዲፕሎማቶች፣ ነጋዴዎችና የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች እንደሚሉት ፣ መንግስት ለህዝባዊ ተቃውሞው መነሻ የሆኑትን ችግሮች ለመፍታት እርምጃ አለመውሰዱ፣ በኢትዮጵያ ላይ ዘላቂ የሆነ ልማትና እድገት እንዳይኖር ያደርጋል።