ጥቅምት ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በዲላ የአካባቢው ሹሞች ቀስቅሰው እንዳስነሱት በሚታመነው ግጭት በከተማዋ ከሚገኙ የተለያዩ ብሄረሰቦች ብቻ 23 ሰዎች ሲሞቱ፣ ከገጠሩ ህዝብ ወይም ከጌዲዮ ማህበረሰብ በርካታ ሰዎች ተገድለዋል።
በዲላ፣ ይርጋጨፌ፣ ወናጎና ሌሎችም አካባቢዎች ግጭቱ መስፋፋቱን ተከትሎ ወደ ከተማዋ የገቡት የአጋዚ ወታደሮች በቀጥታ እርምጃ በመውሰድ በርካቶችን ገድለዋል። በርካታ ሱቆች፣ የቡና መፈልፈያዎች፣ ሆቴሎች፣ መኪኖችና ሌሎችም የንግድ ድርጅቶች ተቃጥለዋል። በርካታ ዜጎችም ተፈናቅለዋል።
የአካባቢው ፖሊሶችና አስተዳዳሪዎች በግጭቱ እጃቸው እንዳለበት ነዋሪዎች አክለው ገልጸዋል። የወረዳው አስተዳዳሪ ግጭቱን ያስነሳው ኦነግ ነው በማለት ችግሩን በሌሎች ለማሳበብ መሞከሩንም ነዋሪዎች አክለው ገልጸዋል። በርካታ ሰዎች እየተያዙ በመታሰር ላይ ቢሆንም፣ የከተማው ነዋሪዎች ግን ለደህንነታችን ዋስትና ካልተሰጠን ስራ አንጀምርም ብለዋል።