ዱባይ አየር ማረፊያ የደረሱ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ወደ አገሪቷ እንዳይገቡ የመግቢያ ፈቃድ ተከለከሉ

ኢሳት (ሚያዚያ 27 ፥ 2016)

በዱባይ አለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ በኩል ወደ ዱባይና የተባበሩት አረብ ኤመሬቶች ለመግባት የተጓዙ 30 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ወደ ኢትዮጵያ ሊባረሩ እንደሆነ ተነገረ።

ገልፍ ኒውስ የተባለ ጋዜጣ ትናንት ማክሰኞ እንደዘገበው ፍላይ ዱባይ በተባለ በዱባይ አየር መንገድ በአንድ የጉዞ መስመር ቲኬት ቆርጠው የተጓዙት ሴቶች ወደ አዲስ አበባ ተገደው እንደሚመለሱ ተነግሯል።

የፍላይ ዱባይ ቃል አቀባይም የኢትዮጵያውያኑ ሴቶች መባረር እውነት እንደሆነ አምነው፣ የሚባረሩበትን ምክንያትም ወደ ኢትዮጵያ የመመለሻ ትኬት ስለሌላቸው ወይም ስለመመለሳቸው ማረጋገጫ ማቅረብ ባለመቻላቸው ወደ ዱባይ እንዲገቡ እንዳልተፈቀደላቸው ገልፍ ኒውስ ለተሰኘ ጋዜጣ ተናግረዋል።

የተባበሩት አረብ ኤመሬትስ ህግ ፥ ጎብኚዎች ቪዛቸው ሳይቃጠል ወደ አገራቸው የመመለስ ግዴታ እንዳለባቸውና ለዚህም ማረጋገጫ ትኬት ማሳየት እንዳለባቸው እንደሚደነግግም ታውቋል።

ገልፍ ኒውስ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው በየቀኑ እስከ 500 የሚደርሱ ህገ-ወጥ የቤት ሰራተኞች ከኢትዮጵያ ወደ ዱባይ በተለያዩ የአውሮፕላን መንገዶችን በመጠቀም እንደሚገቡ ዘግቦ፣ እነዚሁ በቱሪስት ቢዛ የመጡ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ለወኪሎች በህገ-ወጥ መንገድ ከፍተኛ ገንዘብ በመክፈል ወደ ስራ ቪዛ እንደሚያስቀይሩትም በትናንትና ዕትሙ አስነብቧል።

ከዚህ በፊት ወደ ዱባይ የተጓዙት ሌሎች ኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞች “አሞናል” በሚል ሰበብ ወደ አዲስ አበባ መመለስ እንደማይፈልጉና፣ የቆይታ ጊዜያቸውን እንደሚያራዝሙ ተነግሯል።