ኢሳት (የካቲት 17 ፥ 2009)
በአዲስ አበባ ጉብኝትን እያደረጉ ያሉት የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚደንት ሳልባኪር ከኢትዮጵይ ጋር አንዱ የሌላው ሃገር ታጣቂ ቡድኖች እንዳያስተናገዱ የሚያደርግ ስምምነት መፈራረማቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን አርብ ዘግበዋል።
በሁለቱ ሃገራት በድንበር፣ በጸጥታና በነዳጅ አቅርቦት ዙሪያ ተመሳሳይ ስምምነት መድረሳቸውም ታውቋል።
ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን በተለያዩ ጊዜያት ያደረጓቸውን መግባባቶች ተከትሎ የደቡብ ሱዳን አማጺ ቡድን አመራር ሪክ ማቻር ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ መደረጉም ይታወሳል።
ይሁንና የአማጺ ቡድኑ አመራሮች ኢትዮጵያ የወሰደችው እርምጃ በሁለቱ ወገኖች መካከል ሲካሄድ በቆየው ድርድር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን እንዳሳደረ በመግለጽ ላይ ናቸው።
የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ለደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድር ቸልተኝነት አሳይተዋል በተባሉበት በዚሁ ወቅት አሜሪካ ወደ ደቡብ ሱዳን ልዑካን በመላክ የሁለቱ ወገኖች ስምምነት ዕልባት እንዲያገኝ ጥረት መጀመሩም ታውቋል።
በአዲስ አበባ የሚገኙ ፕሬዚደንት ሳልባኪር በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ይመክራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ለመረዳት ተችሏል።