(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 26/2010)
የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የነበረው ዮናታን ተስፋዬ ዛሬ ከወህኒ ተለቀቀ።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌንና የኢትዮጵያ አየር ሃይል አብራሪዎችን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ አስረኞች ግን አሁንም በወህኒ ቤት ይገኛሉ።
በመንግስት ተግባራዊ በተደረገው የምህረት ርምጃ ለመፈታት ይቅርታ መጠየቅ እንዳለበት የተነገረው ዮናታን ተስፋዬ ይቅርታ አልጠይቅም በማለቱ ለሳምንታት በተጨማሪ እስር ቤት ቆይቷል።
ፈርመህ ውጣ ተብሎ ሲጠየቅ “እኔ ወንጀል አልፈፀምኩም፣ የተፈረደብኝ በማምነውና ስወጣም በምሰራው ጉዳይ ነው” በማለት እስከመጨረሻም በአቋሙ ጸንቶ ዛሬ ከቃሊቲ ወህኒ ቤት ወጥቷል።
የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የነበረው ዮናታን ተስፋዬ ወደ ወህኒ የተጋዘው ከኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ ጋር በተያያዘ በማህበራዊ ገጹ ላይ በሰጠው አስተያየት መሆኑም ተመልክቷል።
ዮናታን ተስፋዬ በወቅቱ አስተላለፈ የተባለው እና በማስረጃነት የቀረበበት ጽሁፍ ወጣቶቹ ሊገድሏቸው በሚሄዱት ታጣቂዎች ላይ መንገድ እንዲዘጉ የሚጠይቅ መሆኑንም መረዳት ተችሏል።
ዮናታን ይህ መልዕክቱ በፍርድ ቤት በማስረጃነት ሲቀርብበት ከማስተባበል ይልቅ ሕዝብ ማለቅ ስለሌበት ያደረኩት ትክክል ነበር ሲል ተከራክሯል።
“ሕዝብ መሞት ስለሌለበት ማድረግ ያለበት ይህን ነው። ወንጀል አይደለም፣ አስተላልፌያለሁ፣ አሁንም አስተላልፋለሁ፣ መንገድ መዘጋቱ ብቻ አይደለም ሕዝብን ከጭፍጨፋ ለማዳን ድልድይም ይሰበር፣ ከመንገድና ድልድይ የሚበልጠው የሰው ሕይወት ነው፣ ድልድዩን ነገ እንሰራዋለን!” በማለት መከራከሩም ታውቋል።
በዚህም የ6 ዓመት ከ6 ወራት እስራት የተፈረደበት ዮናታን ተስፋዬ ፣ክሱ ተሻሽሎ እስራቱ ወደ 3 ዓመት ከ6 ወር ዝቅ ብሎለትም ነበር።
የእስራት ጊዜውን ሲጨርስም ከሁለት ወራት ያነሰ ጊዜ የቀረው ዮናታን ተስፋዬ በመጨረሻም በአቋሙ እንደጸና ዛሬ ከወህኒ ቤት ወጥቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የግንቦት 7 ዋና ጸሃፊ የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እና የኢትዮጵያ አየር ሃይል አብራሪዎች እነ የመቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ እንዲሁም የሰማያዊ ፓርቲ የጎንደር አስተባባሪ የነበረው አንጋው ተገኝ አና አባሪዎቹን ጨምሮ በርካታ የፖለቲካ እስረኞች አሁንም ከወህኒ አለተለቀቁም።