ግንቦት ፲፯ ( አሥራ ሰባት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የነበረው ወጣቱ ፖለቲከኛ ዮናታን ታስፋየ ፌስቡክ ላይ በሚጽፋቸው ጽሁፎች ወንጀለኛ ተብሎ በከፍተኛው ፍርድ ቤት የ6 አመታት ከ3 ወር እስር ተፈርዶበታል።
ዮናታን በሰላማዊ ትግል ፍጹም የሚያምን ወጣት እንደነበር የሚናገሩት የቅርብ ጓደኞቹ፣ እንደሱ የፖለቲካ እምነት ቢሆን ኖሮ እንኳንስ እስር ቤት ሊያስገባው፣ ሰላማዊነቱ፣ የሰላም ተሸላሚ ባስደረገው ነበር በማለት፣ የቀረበበትን ውንጀለና የተሰጠውን ፍርድ ኮንነዋል።
በእድሜ የገፉ እና በእርሱ የሚተዳደሩ እናቱን ትቶ ለእስር የተዳረገው ዮናታን፣ የተለያዩ ሰብአዊነት ያላቸውን ሰራዎች በመስራትም ይታወቃል። ዮናታን በመጀመሪያ የቀረበበት የሽብርተኝነት ክስ ቢሆንም ፣ በሁዋላ ላይ ክሱ ወደ ማነሳሳት ተለውጦለታል፡ ይሁን እንጅ ይህም ክስ ቢሆን፣ ከቅጣት አላደነውም።
ወጣት ዮናታን ክሱን በበቂ ሁኔታ ተከላክሏል። ታዋቂ ፖለቲከኞች የሆኑትን አቶ በቀለ ገርባ፣ ዶ/ር መረራ ጉዲና እና ታዋቂውን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ጨምሮ የተለያዩ የመከላከያ ምስክሮችን አቅርቦ አሰምቷል።
በዮናታን ላይ የተላለፈው የፖለቲካ ውሳኔ እንጅ የፍርድ ቤት ውሳኔ አይደለም የሚሉት ጓደኞቹ፣ በእድሜ የገፉት የህወሃት/ኢህአዴግ መሪዎች ነገ አገሪቱን ተረክበው ሊመሩ የሚችሉትን ወጣቶች፣ በተቀናቃኝነት በመፈረጅ እስር ቤት እያስገቡ አእምሮዋቸውንና በራስ መተማመናቸውን ለመግደል እየሰሩ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ላይ የተወሰነበት ውሳኔ የፕሬስ አፈና በኢትዮጵያ ተባብሶ መቀጠሉን ማሳያ ነው ሲል ሲፒጄ መግለጫ አወጣ
የቀድሞው የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ላይ በፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት የተወሰነበት የጥፋተኝነት ብይን በአገሪቱ የፕሬስ አፈናው ተባብሶ መቀጠሉን ማሳያ ነው ሲል ዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ሲፒጄ (CPJ) አስታውቋል።
የጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ጠበቃ የሆኑት አቶ አመሃ መኮንን ”ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው በአንቀጽ 257 ሀ እና መ ሕግ ተላልፈሃል የሚል ክስ ቀርቦበታል። በክሱ ላይ ከጋዜጠኛ አበበ ገላው ጋር በግል መለክቶችን ተለዋውጠሃል፣ ከጋዜጠኛ አበበ ገላው ”አሁን የተሻለ የትግል ስልት ነው” የሚል መልክት ተቀብሏል የሚል ክስ የቀረበበት ሲሆን ደንበኛዬ ግን ይህን አለመፈጸሙን ምላስሽ ሰጥቷል” ብለዋል። ጋዜጠኛ አበበ ገላው በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ላይ ተቃውሞ ማሰማቱ ይታወሳል።
ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ከዲሴንበር እኤአ 25 ቀን 2015. ጀምሮ ጉዳዩ ለተደጋጋሚ ጊዜያት ሲራዘም ቆይቷል። በጋዜጠናው ላይ የቀረበበት የሽብርተኝነት ክስ መሆኑንም ዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ሲፒጄ (CPJ) አስታውቋል።
”በጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ላይ የቀረቡበት ውንጀላዎች የሚያሳየው ነገር ቢኖር አስቂኝ መሆኑንና የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ለጋዜጠኞች ሙያ ክብር የሌላቸው መሆኑን እንዲሁም ጋዜጠኞችን ለማፈን ምን ያህል ዝግጁ መሆናቸውን ማሳያ ነው። እኛ የታሰሩ ጋዜጠኞች በሙሉ ከእስራት ተፈተው ካለምንም ጣልቃገብነት ወደ ቀድሞ ሥራቸው እንዲመለሱ ለባለስልጣናቱ ጥሪያችንን እናቀርባለን።” ሲሉ ወ/ሮ አንጄላ ክዊንታ መግለጫ ሰጥተዋል።