ጥር ፬ (አራት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሂውማን ራይትስ ወች የአለምን የሰብአዊ መብት አያያዝ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ባለፈው የፈረንጆች አመት በኢትዮጵያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውንና በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ መታሰራቸውን ገልጿል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተነሳ ዜጎች መብታቸው መገደቡ ብቻ ሳይሆን፣ አሁንም ድረስ ለቀጠለው አፈና ተዳርገዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈናን መፍቀዱ ብቻ ሳይሆን፣ ዜጎች ማህበራዊ የመገናኛ መንገዶችን እንዳይጠቀሙና ከውጭ አገራት ቡድኖች ጋር ግንኙነት እንዳያደርጉ ይከለክላል።
የጸጥታ ሃይሎች በኦሮምያና በአማራ ክልሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከመግደላቸውም በተጨማሪ በእስር ላይ የነበሩትም ቢሆን በእስር ቤት ውስጥ ስቃይ (ቶርቸር) ተፈጽሞባቸዋል። ገዢው ፓርቲ የጸጥታ ሃይሎቹ የፈጸሙትን ወንጀል ለማጣራትም ሆነ አለማቀፍ ቡድን ጉዳዩን እንደሚረምር የቀረበለትን ጥሪ አልተቀበለም።
“ግልጽ ያልሆነ ታሃድሶ እናደርጋለን የሚል ቃል መግባት ብቻውን በቂ አይደለም የሚሉት የሂውማን ራይትስ ወች የአፍሪካ ተመራማሪ ፊሊክስ ሆርን፣ መንግስት መሰረታዊ የሆኑ መብቶችን እንዲመልስና ለሚደርስበት ትችት በሚሰጠው የአጸፋ እርምጃ ተጨማሪ የመብት ጥሰቶችን ከሚፈጽም ይልቅ ትርጉም ትርጉም ያለው ውይይት እንዲያደርግ” መክረዋል።
ድርጅቱ በ687 ገጽ ሪፖርቱ በ90 አገራት የሚታዩ የመብት ጥሰቶች ይዘረዝራል።